አገር ለማተራመስ ያለመ የምሁራን፣ የሚዲያ ባለቤቶችና አክቲቪስቶች ህቡዕ ቡድን ተያዘ

በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር፣ በአዳማና በድሬዳዋ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ኢላማ ያደረገ ጥቃቶች በመፈጸም ሀገራዊ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረሐይል  አስታወቀ፡፡

የጋራ ግብረ ሐይሉ ለመገናኛ ብዙኅን  በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣  በአማራና በሌሎች ክልሎች ውስጥ መቀመጫቸውን ያደረጉ እንዲሁም አዲስ አበባ ጭምር የሚገኙ ምሁራን፣ የሚዲያ ባለቤቶችና አክቲቪስቶችን ያካተተ ህቡዕ መዋቅር በምስጢር ሲንቀሳቀስ እንደነበር ተደርሶበታል።

ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፣ ፕሮፌሰር ማዕረጉ ቢያበይን፣ ዶ/ር መሰረት፣ ወርቁ ተስፋዬ ወ/ማርያም፣ ተስፋዬ የኋላሸት ፋሲል፣ ሰለሞን ልመንህ ከተማና መንበረ የተባሉ ግለሠቦችም በህቡዕ አደረጃጀቱ ሲሳተፉና ሲያስተባብሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል በከፍተኛ የባለቤትነትና የሐላፊነት መንፈስ የሚንቀሳቀሰውን ሰፊውን የአማራን ሕዝብ የማይወክሉት እና አሁን የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ያልተመቻቸው እነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖች ኅብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ጭቆና ውስጥ ይገኛል የሚል ቅስቀሳ በማድረግ  በሃይማኖት፣ በብሔር እንዲሁም ከእኛ ውጪ ሀገሪቷን ሌላ ማስተዳደር የለበትም በሚል የፖለቲካ ፅንፈኝነት ዓላማ ዙሪያ ደጋፊዎችን ለማሰባሰብ እየሞከሩ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡

በዚህም ሕዝቡን ነጻ እናወጣለን የሚል የአመጽ እንቅስቃሴ ለማካሄድ ሲደራጁና ሀገሪቱን ዳግም ወደነበረችበት ቀውስ ለመመለስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም ጠቁሟል።

ይህንን አላማቸውን ከግብ ለማድረስ በአማራ ክልል ውስጥ በሁሉም ስፍራዎችና በአዲስ አበባ እንዲሁም በሀገሪቷ በሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን በአካባቢዎቹ ከሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች ጋር አስተሳስሮ የማደራጀት ሥራዎች ሢሠሩ እንደነበር መግለጫው አስታውቋል።

በተቀናጀ መልኩ ህቡዕ ወታደራዊ ክንፍ በማደራጀት በጦር መሣሪያ የታገዘ የከተማ ላይ ጥቃት የመፈፀም እቅድ እንደነበራቸው፤ በተለይ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ባለስልጣናት ላይ ጥቃት በመፈፀም ሕዝቡን የማሸበር ተልዕኮ አንግበው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን የጋራ ግብረሐይሉ መግለጫ ጠቁሟል፡፡

ከላይ በተገለጹት ህቡዕ አመራሮች የተዋቀረው የአዲስ አበባው የአደረጃጀቱ ክንፍ በየክፍለ ከተማው ለዘረጋው መዋቅሩ በርካታ የተለያዩ የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያዎች፣ተቀጣጣይ ፈንጂዎችና ቦምቦችን ወደ ከተማዋ ማስገባቱንም መግለጫው አስታውቋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ግዛት የተባለ ባህርዳር ዙሪያ ቁንዝላ አካባቢ መቀመጫውን ያደረገና በአዲስ ውስጥ ለሚገኘው ህቡዕ ክንፍ የተለያዩ ሎጀስቲክስ የሚያቀርብ ግለሰብ በርካታ የእጅ ቦምብ በተለያዩ ክፍለ ከተማዎች ለሚገኙት የቡድኑ አባላት እንዲያስረክብ አቅጣጫ የተሰጠው ቢሆንም፤ በተደረገውቨ ክትትል በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል፡፡

See also  የሚሌ ቀጠሮ - የባቲ ዘመቻ

በተጨማሪም አዲስ አበባ ጣፎ አካባቢ በሚገኝ የቡድኑ አስተባባሪ በሆነው ዳዊት አባቡ ቢተው እና አዲስ አበባ ካራ ኣሎ አካባቢ ነዋሪ በሆነው ታደሰ ወይነው ተሰማ ላይ በተደረገው ክትትል የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችና የወታደር ዩኒፎርሞች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ግብረሐይሉ ለመገናኛ ብዙኅን በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ሙሉቀን ወንዴ ቢተው ፣ ቴዎድሮስ ተሾመ አየነውና ሌሎችም በህቡዕ አደረጃጃቱ በነበራቸው ተሳትፎ መያዛቸውን ጠቁሟል፡፡

በህቡዕ አደረጃጀቱ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥርር ስር የማዋሉ ተግባር በተቀናጀ መንገድ መቀጠሉን ያመለከተው የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረሐይሉ መግለጫ፤ በቀጣይ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃችን ለኅብረተሰቡ ተከታትሎ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply