የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሳይንሳዊ መንገድ ያዘጋጃቸውን የባህል መድኃኒቶች፤ ሰው ላይ ሊሞክር ነው

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባህል መድኃኒቶችን በሳይንሳዊ መንገድ እያዘጋጀ መሆኑንና በተያዘው ዓመት በሳይንሳዊ መንገድ የተቀመሙ ሦስት የባህል መድኃኒቶች በሰዎች ላይ እንደሚሞከር አስታውቋል።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ የአንኮበር ቤተ መንግሥት የሚገኝበት አከባቢ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ሊባል በሚችል መልኩ ለመድኃኒት ቅመማ የሚውሉ ዕፅዋት የሚገኙበት ሥፍራ እንደሆነ መለየቱን ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው፥ የዕፅዋቱን ቅመማ እና መድኃኒትነት የሚያውቁ ረጅም ዕድሜ ያላቸው አባቶች እና እናቶች አሁንም በአካባቢው መኖራቸውን እንደ ዕድል በመጠቀም አብሮ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። 

የባሕላዊ መድኃኒቶችን የአቀማመም ሥልት በማጥናት ሳይንስ በሚቀበለው መልኩ ለማድረግ የተለያዩ ምርምሮች እየተሠሩ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤  በርካታ መድኃኒቶች በቅመማ እና በሙከራ ደረጃ እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።

በአይጦች እና በሌሎች ከሰው ጋር ተመሳሳይ የሰውነት ሥርዓት ባላቸው እንስሳት ላይ ሙከራቸው ተጠናቆ በሰው ላይ ሊሞከሩ የተዘጋጁ ሦስት መድኃኒቶች በያዝነው ዓመት ሙከራቸው ይጠናቀቃልም ብለዋል።

መድኃኒቶቹ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሙከራ ደረጃዎችን ሲያጠናቅቁ ወደ ምርት እንደሚገቡ የተገለጸ ሲሆን ለምን በሽታ መድኃኒትነት የተዘጋጁ እንደሆኑ በዘገባው አልተጠቀሰም።

See also  ትህነግ ያፈረሰውን የጀግኖች ልጆች ማብቂያ ተቋም በቋሚነት ለመርዳት ዲያስፖራዎች ቃል ገቡ

Leave a Reply