ተበድለን እያለ እንደበዳይ መታየት እስከመቸ?

– መልዕክቱ ለሚመለከታቸዉ ብቻ ነዉ

እንኳን የ አለም አቀፉ ማህበረሰብ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊያዊ ጭምር ዛሬም ድረስ የአማራ ክልል በወረራ ስር እንደሚገኝ በቂ መረጃ የለዉም ወይም እንዲኖረዉ አይፈልግም!

የአለምአቀፉ ማህበረሰብ እና ሚዲያወቻቸዉ ከራሳቸዉ አላማ ተነስተዉ በገባንበት የርስበርስ ጦርነት ስለደረሰዉ ጉዳት መናገርና መዘገብ የሚፈልጉት ትግራይ ዉስጥ ደረሰ ስለሚሉት በደል ብቻ ነዉ። በዚህ ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልልሎች የደረሰዉ ዉድመት በትግራይ ክልል ደረሰ ከሚሉት ዉድመትና ጥፋት ሊበልጥ ካልሆነ በስተቀር የሚያንስ አይደለም። ነገር ግን እነዚህ ወገኖች የአማራና አፋር በደል አይታያቸዉም፣ስለሆነም ሊያነሱት አይፈልጉም።

እነዚህ የዉጭ ሚዲያወችና መንግስታት ዛሬም ድረስ በርካታ የአማራ አካባቢወች በትግራይ ወረራ ዉስጥ እንደሚገኙ አንድም በቂ ግንዛቤ የላቸዉም ሁለትም እንደለመዱት ሀቁን መናገር አይፈልጉም።

ሌላዉ ቀርቶ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊም ቢሆን ዛሬም ድረስ በርካታ የአማራ አካባቢወች በተለይም ቆቦ በከፊል፣ ራያ በሙሉ፥ ከፊል ዋግ፣ ከፊል አደርቃይ፣ሙሉ ጠለምተሰ በወያኔ ወረራ ስር እንደሚገኙ በቂ ግንዛቤ ያለዉ አልመሰለኝም። ዛሬ ላይ ከነዚህ በወረራ ከተያዙ አካባቢወች የተፈናቀሉ በመቶ ሽሆች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በዋግ፣ሰሜን ወሎና ደባርቅ በመሳሰሉት በረሀዎችና የመጠለያ ጣብያዎች ተጠልለዉ ይገኛሉ። ገራሚዉ ነገር ሁሉም ተፈናቃዮች አሸንድየና ሶለል አክባሪዎች ነበሩ። እንዴት አሳልፈዉት ይሆን?

ለመሆኑ እነዚህ በወያኔ ወረራ እንደተያዙ የቀጠሉትና ከነዚህ አካባቢዎች ተፈናቅሎ ያለዉ በርካታ የአማራ ህዝብ በአለምአቀፉም ይሁን በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተገቢዉን ግንዛቤና ትኩረት አግኝተዉ መፍትሄ እንዲሰጠዉ ማድረግ ያልተቻለዉ ለምንድን ነዉ? መፍትሄዉ ይቅርና ቢያንስ ግን ዛሬም ድረስ በርካታ የአማራ መሬትና ህዝብ በወያኔ ወረራ ስር እንዳሚገኝ እንዲሁም በርካታ ህዝብ ከነዚህ አካባቢወች ተፈናቅሎ እንደሚገኝ በሚመለከታቸዉ ወገኖች ሁሉ በቂ ግንዛቤ እንዲያዝ ማድረግ ያልቻልነዉ ለምንድን ነዉ?

ለሁሉም አማራ እንዲህ ተበድሎ እያለ እንደበዳይ፣ ተወሮ እያለ እንደወራሪ፣ተፈናቅሎ እያለ እንደ አፈናቃይ የሚታየዉ በሁለት ምክንያቶች ነዉ። የመጀመሪያዉ ምክንያት ትላንትም ሆነ ዛሬ ለ አማራ ህዝብ ቀናኢ አመለካከት የሌላቸዉ የዉጭም ሆነ የአገር ዉስጥ ሀይሎች የአማራ በደልና መገፋት ለነሱ ምናቸዉም ስላልሆነ እዉነቱን ቢያዉቁም ስለ እዉነት ብለዉ ከአማራ ህዝብ ጎን መቆም ስለማይፈልጉ ነዉ። እንዴዉም እነዚህ ወገኖች የአማራን መከራ የደስታ ምንጫቸዉ አድርገዉ ሊዝናኑበት ይፈልጋሉ።

See also  «በአገሩ መከላከያ ላይ አፉን የሚከፍት ሕዝብ የለም፤ መንግስትም አይታገስም» ክብር ለመከላከያ ሰራዊት!!

ሁለተኛዉና ዋነኛዉ ምክንያት ግን የራሳችን (አማራዎች) ድክመት ነዉ። የአማራ ኢሌት በሚገባዉ ልክ ለአለምአቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ለኢትዮጵያዊያን ዛሬም ድረስ በርካታ የአማራ አካባቢዎች በወያኔ ወረራ ስር እንደሚገኙና ከነዚህ አካባቢወች በመቶ ሽህ የሚቆጠር ህዝብ ተፈናቅሎ እንደሚገኝ በልኩ ግንዛቤ መፍጠር አልቻልንም። በመሆኑም ዛሬም ላይ አማራ በወያኔ ወረራ ስር እንደሚገኝ በቂ ግንዛቤ ያለዉ ኢትዮጵያዊ ብዙ አይደለም። እንዴዉም አንዳንዴ ጦርነቱ ሲቆም አማራ ነፃ እንደወጣ አድርጎ ግንዛቤ የተያዘ ይመስለኛል።

ዛሬም ድረስ አማራ በወረራ ስር እንደሚገኝ እንዲህ ደካማ ግንዛቤ እንዲያዝ የተደረገዉ በአማራ ኢሊት ድክመት መሆኑ እንደተጠበቀ ሁኖ፣ በተለይም ደግሞ በክልሉ መንግስት የተሰራዉ የህዝብ ግንኙነት ስራ ደካማ በመሆኑ ነዉ ብየ አምናለሁ። አንዳንዴማ እኮ በወረራ ስር መሆናችንንም የተረሳ ይመስላል። ዛሬም ድረስ በወያኔ ወረራ ስር እያለን ወያኔ ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ ነዉ እንላለን፣ግን እኮ ዛሬም በወረራ ስር ነን። በመሆኑም ትኩረታችን ተጨማሪ ወረራ እንዳይመጣ እንጅ በወረራ ስር ያሉትን ህዝቦች እንዴት ነፃ እናዉጣ የሚለዉ አማራዊ አጀንዳ የተተወ እስኪመስል ድረስ ተዘናግተናል።

በመጨረሻም በሰሞኑ የሻደይ ዝግጅት አቶ ደመቀና ዶ/ር ይልቃል ከእንግዲህ ይበቃል፣ በወረራ ስር ያሉት የአማራ አካባቢዎች ካሁን በሁዋላ በወረራ ስር የሚቆዩበት ሁኔታ አይኖርም ሲሉ የሰማሁ መሰለኝ። ጥሩ ነዉ! ግን ይች አባባል መቸ ነበር የተባለችዉ? ለሁሉም ከፍተኛ መሪዎቹ ያላችሁት ቃል በተግባር ዉሎ ወገኖቻችን ከወረራ ነፃ ወጥተዉ ማየት የሁላችንም ምኞት ነዉ። ስጋቴ ንግግሩ ለመድረክ ፍጆታ ብቻ ሁኖ እንዳይቀር ነዉ። ይሄን ማለቴ ካሁን በፊትም ቃሏ ተብላ ስለነበረ ነዉ።

ለሁሉም ካሁን በሁዋላ ዛሬም አማራ በወያኔ ወረራ ስር እንደሚገኝ እንዲሁም በርካታ ህዝብ ተፈናቅሎ እንደሚገኝ ለሚመለከተዉ ሁሉ እንደ አዲስ ማሰረዳት ያለብን ይመስለኛል። እዉነቱን ከማሳወቅ ዝም በማለታችን ወይም በመፋዘዛችን አማራ ተወሮ እያለ እንደ ወራሪ፣ተፈናቅሎ እያለ እንደ አፈናቃይ ፣ በአጠቃላይ ተበድሎ እያለ እንደበዳይ እየታየ ነዉ። ይህ የሆነዉ ደግሞ በአማራ ኢሌት ድክመት ነዉ በተለይም የፖለቲካ ኢሌቱ።

See also  እነሆ የድሉ ባለቤቶች

Via Chuchu Alebachew FB

Leave a Reply