እጅጋየሁ ዲባባ (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ተበረከተላት፤ “አይገባኝም አመሰግናለሁ”

ዘመን የማይሽራቸው ውብ አገራዊ ይዘት ላይ የሚየጠነጥኑ ድንቅ ስራዎቿን ያበርከተችው፣ በፍቅርም ቢሆን ጥልቅ ሃሳብና ድንቅ ግጥም ያካተቱ ዘፈኖችን ያቀረብችው ጂጂ ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጣት። ጂጂ “አልጠበኩትም፣ አይገባኝም።፡አመስግናለሁ” ስትል ለዚህ ታላቅ ክብር ያበቃትን ዩኒቨርስቲና የኢትዮጵያ ህዝብ አመስግናለች።

ዩኒቨርሲቲው በዛሬው እለት በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ባስመረቀበት ወቅት ነበር ለአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት መስጠቱን ያወጀው። ወቅት እየጠበቀች አገሯ ላይ መርዝ የማትረጭ፣ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ነኝ በሚል ከማይረባ ቦታ የማትገኘው ጂጂ ” አባይ አባይ” የሚለውና “አደዋ” የሚለው ሙዚቃዋ ከማንምኛውም የሙያ አጋሮቿ ተወዳዳሪ የሌለው ስራዋ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተመስክሮላታል። “አባ አለም ለምኔ” የሚለው ዜማዋ ከመላው የሙዚቃና የግጥም ውቅሩ ጋር በጥቅሉ “መጽሃፍ ነው” በሚል ድርሰቷንና አሳቧን ባለሙያዎች አክብረውላታል። ጂጂ ግን በዚህ ስሟ የገነነውን ያህል ስትመጻደቅ ታይታ አታውቅም። በሞቀበት ዘው ስትል አልታየችም።

“እህ ህ እስመከቼ … እግር ተራመድ” በሚለው ልብን ሰርስሮ በሚገባ ሙዚቃዋ እግርን ” ምን ያንፏቅቀሃል አመድ ላመድ” እያለች ዘረኝነትን የኮነነችበትና የጥበብ ቃና የፈሰሰበት ዘፈኗ የጂጂ ሌላው ዘመን የማይሽረው የመጪው ትውልድ ውርስ የሆነ ዘፈኗ እንደሆነ በተደጋጋሚ ምስክር አግኝታለች።

“ካህኔ የነብሴ አገልጋይ” የሚለው እንደ ጧፍ የሚያቀልጥ ዜማዋና ግጥሙ፣ “ባለ ማረግ ባለማረግ… ” የሚለው ፍቅረኛን የሚያሞካሸው ዘፈኗና በገጠር ኑሮ ምንጩ፣ ጥጆቹ፣ እርሻው …. ለውሳ ያዜማቸው የፍቅር ኑዛዜዋ መላ ፍሰቱ ቢሰሙት የማይጠገብ ምርጥ ስራዋ ነው። ረቀቅ ያለና ባህላዊ ትውስታችንን የማይለቀው ሙዚቃዎቿ ጂጂን ተወዳጅና ተደናቂ ያደረጋት በመሆኑ ይመስላል የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ማግኘቷ የሰደድ ያህል ማህበራዊ ሚዲያው እንዲቀባበለው ሆኗል።

በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ ገብታ የማትዘባርቀው፣ ለጥቅም ብላ የማታምታታዋና ራሷንና ሙያዋን አክብራ የራሷን ኑሮ የምትኖረው ጂጂ ” ይቅርታ” በማለት አጭር የምስጋና ድምጽ መላኳን ገልጻ ምስጋናዋን የፈጣሪን ስም በመጥራት ለሚገባቸው ሁሉ በትህትና፣ በመደነቅና ክብሯን በማሳየት አድርሳለች። በቅርቡም መጥታ በአካል የምትወደውን ህዝብ እንደምትቀላቀል አስታውቃለች።

በመርሐ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ/ር) ” አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የሀገሯን ሙዚቃና ባህል እንዲሁም የተወለደችበትን የአገው ህዝብ ባህልና ቋንቋ ለዓለም ህዝብ በማስተዋወቋ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለአርቲስቷ የክብር ዶክትሬት ሲሰጣት ታላቅ ክብር ይሰማዋል” ማለታቸውን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

See also  አተራምሱና ማማ ላይ ... አይ አሜሪካ

“ጂጂን ማክበር ጥበብን ማክበር ነው” ያሉት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ/ር)”ጂጂን ማክበር የኢትዮጵያን ታሪክና ጀግኖችን እንዲሁም ፍቅርንና አንድነትን ማክበር ነው” ጂጂ ለተደረገላት ክብር እንደምትመጥን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲውን በታሪክ ሊያስታውስ የሚችል የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለድንቋ ድምጻዊትና ለጥበብ ንግስት ለአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በሚሰጥበት እለት መሆኑ መርሐ ግብሩን ለየት እንደሚያደርገውም ዶክተር ጋርዳቸው አስታውቀዋል።


Leave a Reply