ለመሬትን ስጋት የሆነው አዲሱ ፕላኔት፤ ሙቀቱ 2,000 ዲግሪ ሴልሺየስ ይደርሳል

የአውሮፓ የህዋ ሳይንስ ድርጅት አዲስ ፕላኔት መገኘቱን በቅርቡ አስታውቋል። በአይነቱ ለየት ያለ ነው የተባለው ይህ  ፕላኔት ከፀሀይ ስርዓት / Solar system / ውጭ ሲሆን፤ እጅግ  ሞቃታማ እና አንፀባራቂ መሆኑም ተገልጿል።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት የአዲሱን ፕላኔት ባህሪያት እና  በምንኖርባት ምድር ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ይቃኛል ።
ስለ ስርዓተ ፀሀይ  /Solar system / ሲነሳ ፀሀይን ፣በፀሀይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ስምንት ፕላኔቶችን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ  ጨረቃዎች እና በሚሊዮን ሌሎች ክዋክብትን /አስትሮይድ ፣ኮሜቶች እና ሜትሮፕዶች/ ያጠቃልላል።   የሚያጠቃልል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። እነዚህም በአብዛኛው የፀሀይ ብርሃንን በውስጣቸው የሚያስቀሩ እና በትንሹ መልሰው የሚያንፀባርቁ  ናቸው። 
ከጎርጎሪያኑ 1990ዎቹ   ጀምሮ  ግን ከፀሀይ ስርዓት ውጭ የሆኑ ሌሎች ፕላኔቶች  በእንግሊዝኛው አጠራር /Exoplanates/መኖራቸውን  የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች  ይፋ አድርገዋል።12 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዓመት ዕድሜ እንዳላቸው የሚነገርላቸው እነዚህ ፕላኔቶች  በሌሎች  ፀሀይ መሰል ክዋክብት ዙሪያ የሚሸከረከሩ እና የራሳቸው ምህዋር ያላቸው ናቸው።
 የአውሮፓ የህዋ ሳይንስ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መረጃ  ደግሞ ከፀሀይ ስርዓት ውጭ  የሆነ ነገር ግን ለየት ያለ አዲስ ፕላኔት  መገኘቱን  ይፋ አድርጓል። 
አዲሱን ግኝት በተመለከተ ያነጋገርናቸው  የዓለም አቀፉ የክዋክብት ምርምር  ህብረት/ International Astrological Union / ምክትል ፕሬዚዳንት እና የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ሰለሞን በላይ  እንደሚሉት ምንም እንኳ አዲሱ ፕላኔት እጅግ ሞቃታማ እና ህይወት ላለው ነገር  ምቹ መኖሪያ ባይሆንም የሰው ልጆችን ከመሬት ውጭ በሌሎች ፕላኔቶች  ለማኖር የሚደረገውን ምርምር የሚያግዝ ነው።


በአይነቱ ፍፁም የተለዬ ነው የተባለው ይህ ፕላኔት LTT9779b በመባል የሚጠራ ሲሆን፤ እጅግ  ሞቃታማ  እና እንደመስታዋት የሚያንፀባርቅ መሆኑን ተመራማሪዎች ገልፀዋል። 
LTT9779b  ፕላኔት ለመጀመሪያ ጊዜ  በጎርጎሪያኑ  2020  ዓ/ም በአሜሪካው የጠፈር ምርምር ጣቢያ በእንግሊዝኛው ምህፃሩ ናሳ በኩል ቢሆንም፤ ዝርዝር ባህሪያቷን  የየያዙት  የቅርብ ጊዜ ግኝቶች  ግን በአውሮፓ የጠፈር ምርምር ጣቢያ  ተከታታይ ጥናት ዳብረው የወጡ ናቸው ተብሏል።
ከመሬት 260 የብርሃን ዓመታት ያህል የሚርቀው ይህ ፕላኔት  2,000 ዲግሪ ሴልሺየስ (ከ 3,600 ዲግሪ ፋራናይት በላይ) የሙቀት መጠን ያለው እና ብርጭቆ መሳይ ነገሮችን እንዲሁም ብረቶችን በማቅለጥ ወደ ደመናነት የሚቀይር እና ብረት ሊያዘንብ የሚችል ነው። ይህንን እጅግ ሞቃታማ እና አንፀባራቂ ፕላኔት ተመራማሪዎች «መኖር የሌለባት ፕላኔት» ሲሉ ገልፀዋታል።ዶክተር ሶለሞንም በሁለት ምክንያቶች ማለትም፤ አንደኛ የፕላኔቷ ሙቀት በዓፅናፈ ዓለም ወይም ዩንቨርስ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ በሁለተኛ ደረጃ ለየትኛውም ህይወት ላለው ነገር በመኖሪያነት ሊያገለግል የማይችል በመሆኑ ሀሳቡን ይጋሩታል። 

Exoplaneten


አዲሷ ፕላኔት በፀሀይ ዙሪያ በራሳቸው ምህዋር ከሚሽከረከሩት ፕላኔቶች መካከል ስምንተኛዋን እና በእድሜ ትንሽ የሆነችውን  ፕላኔት ኔፕቹንን የሚያህል መጠን አላት። ፕላኔቷ  በፀሀይ መሰል ኮከብ ዙሪያ በየ 19 ሰዓቱ በራሷ ምህዋር የምትዞር  ሲሆን፤ያላት ራዴስም በትልቅነቱ ከመሬት 4 ነጥብ 7  ጊዜ የሚልቅ መሆኑን ተመራማሪዎቹ አመልክተዋል።
በሌላ በኩል በስርዓተ ፀሀይ ውስጥ በሌሊት ሰማይን በብርሃን ከምታደምቀው ጨረቃ በተጨማሪ፣  ፕላኔት ቬኑስም በአንፀባራቂነቷ ትጠቀሳለች። ይህቺ ፕላኔት በወፍራም የደመና ሽፋኗ 75% የሚሆነውን የፀሐይ ብርሃን የምታንፀባርቅ ሲሆን፤ በንፅፅር የምንኖርባት  መሬት 30% የሚሆነውን የፀሐይ ብርሃን ብቻ ታንፀባርቃለች።
 የአውሮፓው የህዋ ሳይንስ ድርጅት ከፀሀይ ውጭ ያሉ ፕላኔቶችን በሚያስስበት «ኪዮፕስ» በተባለው ተልዕኮ ባወጣው ዝርዝር መረጃ  አዲሷ ፕላኔት 80% የሚሆነውን ብርሃን ከአቅራቢያዋ ኮከብ በመቀበል መልሳ እንደምታንጸባርቅ አመልክቷል።
ከዚህ አኳያ  አዲሷ ፕላኔት ከቬኑስ አንፀባራቂነት ጋር ሊዛመድ የሚችል አዲስ  ባህሪ ያላት የመጀመሪያዋ  ፕላኔት መሆኗን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ገልፀዋል።
አዲሷ ፕላኔት ምንም እንኳ ከምንኖርባት ፕላኔት፤ ከመሬት  በ260 የብርሃን ዓመት ወይም በብዙ ቢሊዮን ማይል  ርቃ የምትገኝ ቢሆንም፤ ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት የአፅናፈ ሰማይን /ዩንቨርስን/ የሙቀት መጠን እንዲጨምር በማድረግ  የሰው ልጅ በሚኖርባት መሬት ላይ የአየር ሁኔታ እንዲለወጥ በማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። 
ያም ሆኖ ስለ ችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ  የውስብስቧ እና እጅግ ሞቃታማዋ ፕላኔት መገኘት ጠቃሚ  መሆኑን ተመራማሪው ዶክተር ሰለሞን ገልፀዋል።
አብዛኛዎቹ ፕላኔቶች  ብርሃንን ከማንፀባረቅ ይልቅ ወደ ውስጥ የማስቀረት ባህሪ  አላቸው የሚሉት ተመራማሪው፤ ይህም እንደ ጁፒተር በረዷማ የሆኑትን እና እንደ ቬኑስ ያሉ ደመናማ ፕላኔቶችን  ያጠቃልላል።

James Webb Space Telescope, Exoplanet LHS 475 b


አዲሷ ፕላኔት ግን አንፀባራቂ እና የውጫዊ ሽፋኗ እጅግ ሞቃት በመሆኑ  እንደ ቪቪን ፓርሜንቲየር ላሉ የአስትሮኖሚ እና አስትሮፊዚክስ ባለሙያዎች  ፕላኔቷ  ተቃጥላ ከባቢ አየር ውስጥ አለታማ ነገሮችን ልትተው ትችላለች የሚል ስጋት አሳድሯል።  የሙያ  ባልደረባው  ሰርጂዮ ሆዬር ግን ደመናው ብርሃንን በማንፀባረቅ ፕላኔቷ ከመጠን በላይ እንዳትሞቅ እና ትነት እንዳይኖር ያደርጋል ባይ ነው። ነገር ግን ከፍተኛው ብረታ ብረት ፕላኔቷን እና ከባቢ አየርን ከባድ እና ጠንካራ እንደሚያደርገው ገልጿል።ዶክተር ሰለሞን በበኩላቸው የፕላኔቷን ሙቀት ከመሬት ሶስተኛው እና የውጥጠኛው ክፍል ሙቀት ጋር ያመሳስሉታል።ነገር ግን በፕላኔቷ ላይ ቀጣይ እና ጥልቅ  ጥናት ያስፈልጋል ይላሉ።
የሳይንስ ሊቃውንት የፕላኔቷን ባህሪያት ለመወሰን  በ«ኪዮፕስ» ተልዕኮ ዝርዝር ጥናት አድርገዋል። ነገር ግን በአዲሷ ፕላኔት ዙሪያ የሚደረገው ምርምር ያበቃለት እና ዝግ  ባለመሆኑ፤ ከሀብል እና ከጄምስ ዌብ የጠፈር ቴሌስኮፖች ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎችን በመከታተል  ስለፕላኔቷ የተሟላ መረጃ እና ስዕል ለማግኘት አሁንም ድረስ በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
አድማጮች ከስርዓተ ፀሀይ ውጭ በተገኘችው አዲሷ ፕላኔት ላይ የተጠናቀረው የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዝግጅት በዚህ ተጠናቋል።ሳምንት በሌላ ዝግጅት እንጠብቃችኋለን።መልካም ጊዜ።

See also  በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር - የዓለምፀሐይ መኮንን

ፀሀይ ጫኔ ዮሀንስ ገብረ እግዚአብሄር ጀርመን ድምጽ

Leave a Reply