ራስ እምሩን በተመለከተ

የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን ሚያዚያ 27፤2009 የተከበረበትን ዕለት ምክንያት በማድረግ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በዕለቱ (May 5, 2017) “የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታና የባንዳዎች ዕዳ!” በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ ለኅትመት አቅርቦ ነበር፡፡

የጽሁፉ ዓላማ በዚህ መልኩ ቀርቦ ነበር፤

“በየዓመቱ ሚያዝያ 27 የሚከበረው የድል ቀን በኢትዮጵያ የቀን መቁጣሪያ (ካሌንደር) ላይ ሥራ ተዘግቶ እንዲከበር ቢደረግም ትውልዱ የቀደሙ እናትና አባቶቹን የተጋድሎ ታሪክ እንዲያወቅ የሚያስችል የበዓል አከባበር አይታይም፡፡ ዕለቱም እንደአንድ ተራ የረፍት ቀን ያልፋል፡፡ በአንጻሩ አንዳች አገራዊ ፋይዳ የሌላቸው የህወሃት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ … የምሥረታ ቀን እየተባለ በብዙ ሚሊዮን ገንዘብ የሚወጣባቸው ለወራት በዕቅድ ተይዘው የሚደገሱ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ይደረጋል፡፡

“አዲስ አበባ አራት ኪሎ አደባባይ ላይ በሚገኘው የድል ኃውልት ላይ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥና በዕለታዊ የዜና ሽፋን የሚታለፈው ይሄው የድል በዓል፤ ትውልዱ የበዓሉን ፋይዳ በቅጡ እንዳይረዳው አድርጎታል፡፡ የፋሽስት ጣሊያን የአምስት ዓመቱ የወረራ ዘመን በተነሳ ቁጥር የዛሬ ቁንጮ ገዥዎች (የሕወሓት አመራሮች) እንደዘዉጌ ብሄርተኝነታቸው የሚያፍሩበት እንጂ የሚኮሩበት ታሪክ እምብዛም ነው፡፡ ታሪክን በዜግነት ማዕቀፍ ሳይሆን በዘውጋዊ ማንነት ሽንሽኖ ማየት የሚቀላቸው የሕወሓት ሰዎች የኢትዮጵያውያን የድል ቀን የሆነውን ሚያዝያ 27 በየዓመቱ በደበዘዘ መልኩ እንዲከበር ማድረግ መርጠዋል”፡፡

በዕለቱ ያተምነው ጽሁፍ ዋንኛ ዓላማ ይህንኑ የህወሓትን ጠባብና ትውልድ አፍራሽ ጸረ-ኢትዮጵያዊ አሠራር በመቃወም የአርበኞችን ውለታ ለማስታወስ ነበር፡፡ ዘገባውን በጽሞና ላነበበ ሁሉ ግልጽ ሆኖ የሚያገኘው ሃሳብ ይህንኑ ነው፡፡

አገሪቱ የጀግኖች አብቃይ የመሆኗን ያህል በባንዳነት የጎዷት እንዳሉ በጽሁፉ ተመልክቷል፡፡ ጽሁፉ ከጅምላ ፍረጃ በራቀ መልኩ የቀረበ ሲሆን አብዛኛዎቹ የትግራይ ባላባቶች ለጣሊያን የማደራቸውን ያህል እንደ ራስ መስፍን ረዳ ዓይነት ስመጥር ጠንካራ አርበኛ እንደነበሩ በአስረጅነት ቀርቧል፡፡ ከዚህ አንጻር የባንዳነቱ ተግባር በትግራይ ተወላጆች ብቻ ያልተወሰነ መሆኑን ለመግለጽ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “አዳፍኔ” በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መጽሐፍ በመጥቀስ ለባዕድ አገዛዝ አድረው ከጣሊያን መንግሥት ደመወዝ ተቀባዮች የነበሩትን መሳፍንቶችና መኳንንቶችን ዝርዝር አቅርበን ነበር፡፡

See also  ወደር የሌለው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና! ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም

በቀረበው ሠንጠረዥ ላይ የ13 መሳፍንቶችና መኳንንቶች ስም የተዘረዘረ ሲሆን በስም ከተጠቀሱት ውስጥ የራስ እምሩም ይገኝበታል፡፡ ይህንን የጎልጉል ጽሁፍ ያነበቡና የራስ እምሩ የልጅ ልጅ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሳህሉ ሚካኤል እምሩ በራሳቸው፣ በልዑል ራስ እምሩ ቤተሰብና በወዳጆቻቸው ስም ለጎልጉል በላኳቸው መልዕክቶች በታተመው ጽሁፉ ማዘናቸውንና የራስ እምሩ ስም ከሌሎች ባንዳዎች ጋር አብሮ መጠቀሱን በመቃወም እርማት እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

የጎልጉል ስህተት፤

በጽሁፉ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው የጣሊያን ደመወዝ ተከፋይ የሆኑት ሰዎች ዝርዝር የተገኘው ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ከጻፉት “አዳፍኔ” መጽሐፍ ላይ ነው፡፡

መረጃውን ስንጠቅስ ሁለት ስህተቶችን ፈጽመናል፤

  1. መረጃው የተገኘው በጽሁፉ ላይ እንደሰፈረው ከአዳፍኔ መጽሐፍ ገጽ 152 ሳይሆን 151 ላይ ነው፡፡ ሌላው ፕ/ር መስፍን አልቤርቶ ስባኪ (ስባቺ) ብለው የጠቀሱትን መጽሐፍ ሙሉ ዝርዝር መጥቀስ ሲገባን “57” የሚለውን የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር ብቻ መጥቀሳችን ስህተት ነው፡፡ (በመጽሐፉ ገጽ 276 ላይ በዋቢነት እንደተጠቀሰው ፕ/ር መስፍን ዋቢ ያደረጉት መጽሐፍ የሚከተለው ነው፤ አልቤርቶ ስባኪ፤ ትርጉም በእምሻው ዓለማየሁ፣ ኢትዮጵያ፡ በኢጣሊያ ፋሺስት የወረራ ዓመታት፡ 1928-1933፣ አዲስ አበባ፣ 2002)
  2. ፕ/ር መስፍን በአዳፍኔ ገጽ 151 ላይ “ሰንጠረዥ 4 ከኢጣሊያ መንግሥት ደመወዝ ተቀባዮች መሳፍንትና መኳንንት” በማለት የ13 ሰዎችን ስም ያሰፈሩትን እንደወረደ በጥቅስ ምልክት ውስጥ አስገብተን ከማቅረብ ይልቅ “በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ለባዕድ አገዛዝ አድረው (ባንዳ ሆነው) ከጣሊያን መንግስት ደመወዝ ተቀባዮች የነበሩ መሳፍንቶችና መኳንንቶች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-” በማለት በቅንፍ “ባንዳ ሆነው” የሚሉ ቃላት መጨመራችን እንደ ዘገባ አቅራቢ ሚዲያ ስህተት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ለእነዚህ ከላይ ለተዘረዘሩት ሁለት ስህተቶች አቶ ሳህሉ ሚካኤልን፣ የልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ቤተሰቦችና ወዳጆች ይቅርታ ይጠይቃል፡፡

ለወደፊት መደረግ የሚገባው፤

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ጎልጉል የአርበኞችን ውለታ በማሰብ በዕለቱ ያተመው ጽሁፍ ከራሱ ያወጣው ወይም የአንድን ሰው ስም ለማጉደፍ ሆን ብሎ ያተመው ወይም በክፉ መንፈስ በመነሳሳት ያሰራጨው ጽሁፍ አይደለም፡፡

See also  ከተማ ይፍሩ - ያልተነገረላቸዉ የአፍሪቃ አንድነት መስራችና ዲፕሎማት

በጽሁፉ ላይ የሰፈረውን የራስ እምሩን ታሪክ በተመለከተ የልጅ ልጃቸው ሳህሉ ሚካኤል እምሩ የጎልጉል ጽሁፍ ከታተመ በኋላ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ መረጃዎችን በማጣቀስ ይህንን የመቃወሚያ ጽሁፍ አሰራጭተዋል (ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)፡፡ ለጎልጉል የሰጡትን ምላሽ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡ ከዚህም ሌላ ለፕ/ር መስፍን መጽሐፍ ምላሽ የሚሆን የሚከተሉትን ጽሁፎች በአማርኛና በእንግሊዝኛ አውጥተዋል፡፡

እነዚህ የመቃወሚያ ጽሁፎች የፕ/ር መስፍን መጽሐፍ ከታተመ (2007ዓም) በኋላ ወዲያውኑ ሊወጡ የሚገባቸው ነበሩ ብለን እናምናለን፡፡ አሁንም ቢሆን ግን አልረፈደም፡፡ ከዚህ በተሻለ መልኩ ማስረጃዎች በዋቢነት የተጠቀሱበት መጽሐፍ ቢታተም በማለት ለራስ እምሩ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና ለታሪክ አዋቂዎች ሃሳብ እናቀርባለን፤ ይህንን የመሟገትና የመከላከል ኃላፊነት የእነርሱ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ መልኩ ማስረጃዎች ከቀረቡ ወደፊት የሚወጡ ጽሁፎች እነዚህን መጽሓፍትን ያጣቀሱና የተመጣጠኑ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡ ይህም አንድን የመረጃ ምንጭ ብቻ ዋቢ ያደረገ ጽሁፍ ከማውጣት ይታደጋል፤ ለመጪው ትውልድም ትምህርት ሊሆን በሚችል መልኩ በዋቢነት ሊቀመጥ ይችላል ብለን እናምናለን፡፡

ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ኤዲቶሪያል ቦርድ


ሳህሉ ሚካኤል እምሩ ለጎልጉል በላኩት ኢሜይል ተቃውሟቸውን የገለጹት በሚከተሉት ሰዎች ስም መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Woizerit Mamiye Imru, daughter of Ras Imru;
The grandchild of Woizero Yemiserach Imru;
The children of Woizero Martha Imru;
The children of Woizero Hirut and Woizero Yodit Imru;
The children of Lij Mikael Imru; and
The children of Woizero Elleni Imru. The friends of the family who contacted me, or contacted other family members, are too numerous to list here.

(ፎቶዎቹ ከኢንተርኔት የተገኙ ናቸው፡፡ የግራው “ካየሁት ከማስታውሰው” ከሚለው መጽሐፍ ሽፋን የተወሰደ ነው)

Leave a Reply