ምስራቅ ጎጃም ኦፕረኤሽን ተጠናቀቀ፤ የሸሹት መከበባቸው ተሰማ፤ በሰላም ትጥቅ እንዲያወርዱ ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብተዋል

በደብረ ኤሊያስ ስላሴ ገዳም መሽገው የነበሩ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የጸጥታና ደህንነት ግብረሃይል ማስታወቁን ተከትሎ ባካሄድነው ማጣራት የሸሹ መከበባቸውና ሽማግሌዎች በሰላም ጠብመንጃ አውርደው እጅ እንዲሰጡ እየተማጸኑ መሆኑ ተሰምቷል።

ቀደም ሲል ቤተርስቲያኑንና ነዋየ ቅድሳቱ መውደማቸውን እነ መሳይ መኮንን በተደጋጋሚ ሲዘግቡና መረጃ ቲሌቪዥንም ይህንኑ ዘገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም በመጥራት ሲያባዛ እንደነበር ይታወሳል። ይህንኑ መረጃ ተከትሎ ዜጎች አዝነው ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር። መረጃው በኬንያ የተፈጸመ ድርጊትንና በኢትዮጵያ በሌላ አካባቢ የተከሰተን የቆየ ፎቶ ዋቢ በማድረግ የህዝብን ቁጣ እንዲቀሰቅስ ታስቦ ቢሰራጭም የምስራቅ ጎጃም ዞን አገረ ስብከት ዋና አስተዳዳሪ አባ መላከ ሰላም፣ የተባለው አደጋና ጉዳት አለመድረሱን መግለጻቸው መረጋጋት ሊፈጥር ችሏል። ይሁን እንጂ የተሳሳተ መረጃ ሲያቀርቡ የቆዩት አካላት ይህ እስከታተመ ድረስ ማስተባበያ አላሰሙም።

የኢትዮ12 የአዲስ አበባ ተባባሪ እንዳለው የጋራ ደህንነቱ ዝርዝር መረጃ ባያቀርብም፣ ሸሹ የተባሉት ታጣቂዎች ተከበዋል። ከሌላ አቅጣጫ በመጣባቸው ሃይል ተገድበዋል። ጎን ለጎን እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ሽማግሌዎች ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተሰምቷል። ዜናውን ያካፈሉት ወገኖች እንዳሉት አስቀድሞ ሰው ከመሞቱ በፊት በሰላም ሊቋጭ የሜጋብን ጉዳይ ልዩ ዓላማ ያላቸው አካላት ጠልፈውትና ድጋፍ እያደረጉ እዚህ እንዳደረሱት ጠቁመዋል። የተጀመረው ጥረት ይስካል ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል። ከልሉም ሆነ ከፌደራል ዜናውን አስመልክቶ የተባለ ነገር የለም።

ከቤተ ክርስቲያኑ ግርጌ ተሰርቶ የነበረ ምሽግ

“በደብረ ኤሊያስ ጥንታዊ ገዳም ላይና በአካባቢው ኗሪዎች ላይ የጦር ወንጀል እየተፈጸመ ነው!” ሲል ራሱን የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ሲል የሚጠራውና በሻለቃ ዳዊት የሚመራው ግንባር መግለጫ አውጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የጋራ ጸጥታ ሃይሉ ከሰጠው መግለጫ በሁዋላ በአዎንታዊም ሆነ አሉታዊ መልኩ ያለው ነገር የለም።

ከጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠ መግለጫ

በጎጃም ደብረ ኤልያስ ሥላሴ ገዳም መሽገው መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ በነበሩት እስክንድር ነጋና ግብረዓበሮቹ ላይ በተወሰደው እርምጃ ክልሉን የማተራመስ ሴራቸው መክሸፉን  የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ የሚገኘውን የሥላሴ  ገዳም ከለላ በማድረግ መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ በተወሰደው እርምጅ በእስክንድር ነጋና በግብረዓበሮቹ  ለውጊያ ሲውል የነበረው ምሽግ መሰበሩንና በ200 ታጣቂዎችም ላይ እርምጃ መወሰዱን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡ 
የታጣቂ ቡድኑ መሪና አስተባባሪ የነበረው እስክንድር ነጋና ጥቂት ግብረዓበሮቹ  ከአካባቢው ለመሰወር ቢሞክሩም በዋናነት የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ለማዋል እግር በእግር በመከታተል የተቀናጀ ኦፕሬሽን እያካሄዱ መሆኑንም ግብረ ኃይሉ ገልጿል፡፡ 

See also  "መከላከያ ነገ መቀለን በይፋ ይረከባል፤ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱን ይጀምራል"

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ፤ ባልደራስ በሚል የፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን ሲንቀሳቀስ የቆየው እስክንድር ነጋ የተባለው ግለሰብ  የሐሳብ የበላይነትን በማረጋገጥ ዓላማውን ማሳካት ሲሳነው በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ሲሞክር እንደነበር አስታውሷል፡፡

ግለሰቡ ይህ እንዳልተሳካለት ሲያውቅ፤ መንግሥትን በኃይል ለመጣል በማቀድ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተባለ አደረጃጀት በመፍጠር ሽመልስ ስማቸው፣ ሰውመሆን ወረታውና መንበሩ ካሴ ከተባሉ ግብረዓበሮቹ እንዲሁም ከሌሎች ጥቂት የክልሉ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር በመቀናጀትና በህቡዕ በመንቀሳቀስ  ታጣቂዎችን ሲመለምል፣ ሲያደራጅና ስምሪት ሲሰጥ እንደነበር መግለጫው ጠቁሟል። ግንባሩን በሀገር ውስጥ ራሱ ሲመራ በውጭ ደግሞ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ የተባለ ግለሰብ ያስተባብራል ያለው መግለጫው፤ ሁለቱ  በፈጠሩት ትስስር በክልሉ የትጥቅ ትግል በማድረግ ሕዝቡን ወደማያባራ ጦርነት ለማስገባት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ማረጋገጡን አመልክቷል፡፡

መሠረቱን ምዕራብ ጎጃም ቡሬና አባይ በረሃ አካባቢ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግለሰቡ የሃይማኖት ሽፍንና እንደ ከለላ ለመጠቀም ከሌሎች የቡድኑ ታጣቂዎች  ጋር ወደ ምሥራቅ ጎጃም ዞን  ደብረ ኤልያስ ወረዳ በማቅናት  ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በሥላሴ ገዳም አካባቢ ምሽግ ቆፍረው መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል በህቡዕ ሲያሴሩ እንደነበር ያመለከተው የግብረ ኃይሉ መግለጫ፤ በተለይ የገዳሙ አስተዳዳሪ የሆኑትን አባ ኤልሳን ለዚህ ሕገወጥ ተግባር ሲጠቀሙ እንደነበር ጠቅሷል፡፡ አስተዳዳሪውም ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ውጭ በገዳሙ ውስጥ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ከመፍቀድ ባሻገር ከሌሎች መነኮሳት ጋር በማበርና የጦር መሣሪያ ጭምር በማንገብ ከጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ጋር  ተሰማርተው እንደነበርም ጠቁሟል፡፡

መግለጫው አክሎም እነዚህ ጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ሕግ የማስከበር ተልዕኮ ለማደናቀፍ በማለም የዜጎችን ሰላማዊ ሕይወት በሚያስተጓጉሉ ቅስቀሳዎችና ተግባራት ተሰማርተው መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡ በአማራና በወለጋ አዋሳኝ አካባቢዎችም ግጭት እንዲቀሰቀስ ሲያደርጉ እንደነበርም አመልክቷል፡፡

የጥፋት ቡድኑ አባላት ሕገ ወጥ እንቅስቃሴውን እንዲያቆሙና በውይይት ወደ ሰላም እንዲመጡ ከክልል እስከ ወረዳ በሚገኙ አካላት ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም አለመሳካቱን የጠቆመው መግለጫው፤ ይልቁንስ ገዳሙን ምሽግ በማድረግ በአካባቢው አስተዳደር፣ በፖሊስ፣በሚሊሻና በማኅበረሰቡ ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡ በሃይማኖት ሽፋን ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር መታወቁንም አመልክቷል፡፡

See also  በስብሓት ነጋና በሱ የቅርብ ሰዎች ከእስር ቤት ተነጥሎ መፈታት ከአማራ ይልቅ ትልቅ ኪሳራ የሚያደርሰው በወያኔ ላይ ነው

አነዚህ ጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች ከኅብረተሰቡ ባሕልና ዕሴት እንዲሁም ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ባፈነገጠ መንገድ በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ገዳም  ውስጥ ምሽግ በመቆፈር ሕዝቡ ቅዱስ የሚለውን ሥፍራ የጦር አውድማ በማድረግ ለማርከስ ቢጥሩም በዋናነት የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በመቀናጀት በወሰዱት ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ሴራው መክሸፉን ያስታወቀው የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረኃይል፤ በታጣቂዎቹ ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ የተለያዩ ከባድና ቀላል መሣሪያዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁሟል፡፡ 

200 የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ታጣቂዎች  መደምሰሳቸውነና የቀሩትም ከመማረካቸውና ከመሸሻቸው ውጪ፤ ቡድኑ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በሚነዛባቸው የማኅበራዊ ትስስር ገፆች በመንግሥት ጸጥታ አካላት በገዳሙና በምዕመናን ጉዳት እንዳደረሰ ተደርጎ የሚሠራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ እርምጃ በወሰዱበት በዚህ ሕግ የማስከበር ስምሪት የአካባቢው ማኅበረሰብ መረጃ በመስጠትና በሌሎችም መንገዶች ያደረገው ትብብር የሚደነቅ መሆኑን ያመለከተው የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ለዚህም  ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በቀጣይም ክልሉ ከጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች ጸድቶ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲሰፍን ለሚደረገው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ የጋራ ጥረቱንና አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል
ቀን ግንቦት 26/ 2015 ዓ.ም

Leave a Reply