በአማራ ክልል ዝርፊያ መፈጸሙና ንብረት መውደሙ ከመረጋጋት በሁዋላ የሕዝብ አጀንዳ ሆነ

የአማራ ክልል ተፈትሮ የነበረውን ቀውስ ተከትሎ ከፍተኛ አግባብነት የሌላቸው ድርጊቶች እንድተፈጸሙ እየተገለጸ ነው። በሰው ላይ የደረሰው ጉዳት በይፋ በገለልተኛ ወገን ባይጣራም ጉዳቱ ቀላል እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው። ዝርፊያ ተፈጽሟል። ንብረት እንዲወድም ተደርጓል። አሁን ላይ ክልሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ በመግባቱ ህዝብ በሆነውና ባየው ጉዳይ በስፋት እየተነጋገረ እንደሆነ ተሰምቷል።

በድንገት በተባራሪ ጥይት ህይወታቸው ያለፈ በርካታ ንጽሃን፣ “ለምን ትግሉን አልተቀላቀላችሁም በሚልና የመንግስት አጋዥ ነህ” በሚል እርምጃ የተወሰደባቸውና በርካታ ዜጎች መኖራቸውን የሚጠቁሙ አሁንም መፍትሄው ጠብመንጃ በማንሳት በሰላም መወያየት እንደሆነ ይመክራሉ።

የአማራ ክልል ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው ሲናገሩ እንደተሰማው ንብረት ማውደም የክሉን ህዝብ ስራ አጥነት የሚያባብስ፣ አንዳችም ፋይዳ የሌለውና ዓላማ ቢስ ተግባር ነው። ቤታቸው ራሳቸውን ሸሽገው የነበሩና አሁን ሰላም መውረዱን ተከትሎ የወድመውን ንብረት ለመመልከት እድል ያገኙ እጅግ ማዘናቸውን አስታውቀዋል። ንብረት የማውደም ፖለቲካ ጥቅሙና ግቡ ሊገባቸው እንደማይችል አመልክተዋል። ለአብነት በፍሎራ ጣና እና በደቡብ ወሎ የተፈጸመውን ሚዲያው እንደሚከተለው ዘግቧል።

ጣና ፍሎራ አበባ ልማት ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት መኾኑን አስታወቀ

ባሕር ዳር: ነሃሴ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ በአማራ ክልል በነበረው አለመረጋጋት ጣና ፍሎራን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች አራት የኢንቨስትመንት ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በአማራ ክልል በተፈጠረው አለመረጋጋት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡ ከሰሞኑ በባሕርዳርና አካባቢው በነበረው አለመረጋጋት የአበባ ምርት አምራቹ ጣና ፍሎራ እና ሌሎች አራት ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት ለበርካታ ሠራተኞች የሥራ እድል የፈጠሩ፣ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ተቋማት ናቸው፡፡

የጣና ፍሎራ የኢርጌሽን ሱፐርቫይዘር መኳንንት ወርቁ በጣና ፍሎራ ከአሥር ዓመታት በላይ እንደሠራ ነግሮናል፡፡ ጣና ፍሎራ ለበርካታ ዜጎች የሕይወት መሠረት የሆነ ነውም ብሏል፡፡ በጣና ፍሎራ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ በርካታ ሠራተኞች ሕይወት መስርተውበታል፣ ቤተሰብ ደግፈውበታል፡፡ ብዙዎችን አቅፎ የያዘው ተቋም ወድሞብናልም ነው ያለው፡፡

ጦርነት ለማንም እንደማይጠቅምና አውዳሚ መሆኑን የተናገረው መኳንንት በጦርነት ምክንያት ለሀገር ትልቅ አስተዋጽዖ የሚያደርገው ድርጅት ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል ነው ያለው፡፡ ጣና ፍሎራ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ እንደነበረም ተናግሯል፡፡ ችግሮችን በሰላም መፍታት እየተቻለ በተፈጠረው አለመረጋጋት መውደም የሌለበት ድርጅት መውደሙን ነው የገለጸው፡፡

See also  በጀርመን የኤርትራ መንግስት ደጋፊና ተቃዋሚዎች ተጋጭተው 26 ፖሊሶች ጉዳት ደረሰባቸው፤ መቶ ኤርትራውያን ታሰሩ

ካለፈው ውድቀትና ውድመት በመማር ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል፣ ጦርነት ውድመት ከማምጣት ያለፈ ጠቃሚ አይደለምም ብሏል፡፡ ማንኛውም ሰው የጦርነትን አስከፊነት በመረዳት ሰላምን መስበክ እንደሚገባውም ተናግሯል፡፡ የአማራ ክልል ከጦርነት ሳያገግም፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ሳይመለሱ ያለ ክልል ነው ያለው መኳንንት አሁን ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ ክልሉን የበለጠ ይጎደዋል ነው ያለው፡፡ የእርስ በእርስ ችግሮችን በውይይት መፍታት ግድ እንደሚልም ተናግሯል፡፡ ከንግግር ያለፉ አካሄዶች ማኅበረሰብን ይጎዳል ብሏል፡፡ ግጭት የሚያወድመው የራስን ሀብት እንደሆነም ገልጿል፡፡

ጣና ፍሎራ ከፍተኛ ውድመት ስለደረሰበት ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ እንዳደረጋት የተናገረው መኳንንት መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ወጪ እንሚጠይቅም ተናግሯል፡፡ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን ተቋማትን እንደ ግል ሃብት መጠበቅ እንደሚገባም ገልጿል፡፡ ለልጆች ሰላምን ማስተማር ይገባልም ብሏል፡፡

የጣና ፍሎራ ፕሮፓጌሽን ሱፐርቫይዘር ዓለም ፈጠነ በጣና ፍሎራ አሥርት ዓመታትን መሠራቷን ተናግራለች፡፡ ከጣና ፍሎራ በማገኘው ገቢ ደካማ ቤተሰቦቼን አስተዳደርላሁ ነው ያለችው፡፡ አሁን ላይ ግን እንደ ቤተሰብ የምናየው ጣና ፍሎራ ወድሞብናል ብላለች፡፡ ከለበስነው ልብስ ውጭ ምንም ሳንይዝ ሁሉም ጉዳት ደርሶብናል ነው ያለችው፡፡ ድርጅቱም ዘረፋና ወድመት እንደደረሰበት ነው የተናገረችው፡፡

እንደ ሠራተኛም እንደ ድርጅትም ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰው ብላለች፡፡ ሰላም ካለ ሁሉም አለ፣ ሰለም ከሌለ ሁሉም የለም፣ ሁሉንም እንዳናጣ ሰላምን መጠበቅ ይገባል ነው ያለች፡፡ ከጦርነት የሚገኘው ውድመት ብቻ ነውም ብላለች፡፡

የጣና ፍሎራ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጌታቸው ጨርቆስ ጣና ፍሎራ ከ13 ዓመታት በፊት 300 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ተደርጎበት የጀመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጣና ፍሎራ በየአመቱ ከ8 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር የሚያስገኝ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ጣና ፍሎራ አንድ ሺህ ቋሚ ሠራተኞችን ቀጥሮ ሲያሠራ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የደረሰው ጉዳት በባለሙያ የሚገመት ቢሆንም ጣና ፍሎራ እስካሁን ባለው ግምት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሶበታል ነው ያሉት፡፡ የሌሎች ተቋማት ሲጨመር ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ጣና ፍሎራን በፍጥነት ወደ ሥራ ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ጣና ፍሎራ የማኅበሰረብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሰላምን በውይይት ማምጣት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ውይይት የማይፈታው ነገር እንደሌለም ገልጸዋል፡፡

See also  “ዘመን ትውልድን ይገነባል ፤ ትውልድም ዘመንን ይገነባል”

በደቡብ ወሎ ዞን በተፈጠረ አለመረጋጋት በአንዳንድ አካባቢዎች ዘረፋና ውድመት መድረሱን የምሥራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት አባልና የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ሕዝብ እንደማንኛውም አካባቢ ማኅበረሰብ የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር፣ የሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ችግሮች ቢኖሩበትም ከመንግሥት ጋር በመተባበር እንደሚፈታለት ያምናል ሲሉ ዋና አሥተዳዳሪው በመግለጫቸው አስረድተዋል፡፡

እንደ አማራ ሕዝብም የማንነትና የወሰን እንዲሁም የህገ-መንግሥት መሻሻልና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ስለመኖራቸውም አንስተዋል፡፡ እነዚህንም በታቀደ፣ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታለት የሚሻ ታላቅ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡

በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን ሕዝብ መልሶ ለማቋቋም መንግሥት ሰፊ ሥራ እየሠራ ባለበት ሂደት ከጦርነት ማግስት ከሰላም አማራጭ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ህግና ስርዓት እንዲከበርለት ሕዝቡ በሠላማዊ ሰልፍ መጠየቁንም ዋና አስተዳዳሪው አውስተዋል፡፡

በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የተደረገውን የስም ማጥፋት ዘመቻም ሕዝቡ ማውገዙን ገልጸዋል፡፡ መከላከያ የሀገር አለኝታና የሉዓላዊነት መገለጫ ስለመሆኑም ሕዝቡ ከአሁን በፊት አካሂዶት በነበረው ሠላማዊ ሰልፍ ማረጋገጡንም ጠቅሰዋል፡፡

በማዳበሪያና ምርጥ ዘር ስርጭትና የእርሻ ሥራ ወሳኝ የልማት ወቅት ላይ አርሶ አደሩ በተረጋጋ መንገድ ሥራውን እንዳያከናውን በቅርቡ የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች የልማት ሥራውን ከማስተጓጎላቸው በተጨማሪ የማኅበረሰቡን በሠላም ወጥቶ የመግባት እንቅስቃሴ መገደባቸውን ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞንም በምዕራብ አካባቢ ባሉ አንዳንድ ወረዳዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ችግር የንብረት ዘረፋና ውድመት ደርሷል ብለዋል፡፡ በመካነ ሠላም ማረሚያ ቤት ዘረፋና ውድመት ደርሷል፡፡ ኅብረተሰቡንም የማጎሳቆል ሥራ ተሠርቷል፡፡ በአቀስታ ከተማ የመንግሥት ቢሮዎች ኮምፒውተርና ሌሎች የቢሮ ቁሳቁሶች ተዘርፈዋል ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው፡፡ ጃማ ደጎሎ ከተማም ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአማራ ሳይንት ወረዳ ንብረት እንዳይዘረፍና የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ማኅበረሰቡ ተደራጅቶ የመከላከል ሥራ ሠርቷል፡፡ መሃል ሳይንትም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁመዋል ዋና አሥተዳዳሪው፡፡ በወግዲ ወረዳ ጥሩ እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸዋል። አልብኮ ወረዳም ከሌላ አካባቢ ለመዝረፍ የመጣ ቡድን ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

የዞኑ ሕዝብ ያልተገባ እንቅስቃሴን ባለመቀበል መከላከያ ሠራዊት ሕግ እንዲያስከብርለት እየጠየቀ ስለመሆኑ አስረድተዋል። ማዳበሪያም እንዲቀርብለት አርሶ አደሩ እየጠየቀ ይገኛል ብለዋል፡፡

See also  Ethiopia to honor victims of November 3, 2020

የአካባቢው የፀጥታ ኃይልና አሥተዳደር ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በመቀናጀት አለመረጋጋት የገጠማቸውን አካባቢዎች ወደቀደመ ሰላማቸው በመመለስ መደበኛና የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በተለመደው መንገድ እንዲከናወኑ ይደረጋል ብለዋል። መረጃው የደቡብ ወሎ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ነው።


Leave a Reply