ብጉር | Acne vulgaris

  • ብጉር በአብዛኞቻችን ዘንድ የሚታወቅ፤ ወዝ አመንጪ እጢዎች ተከማችተው በሚገኙባቸው የአካል ክፍሎች ላይ (ፊት ፣ ደረት ፣ የላይኛው የጀርባ ክፍል) የሚወጣ የቆዳ ህመም አይነት ነው።
  • ብጉር ከጨቅላ ህጻናት ጀምሮ የሚከሰት ቢሆንም በአብዛኛው ከ12-25 የእድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ላይ ይታያል።
  • ብጉር አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች ላይ የሚከሰት ሲሆን ከወጣትነት የእድሜ ክልል በኋላ (30 እና 40ዎቹ) የሚከሰተው የብጉር አይነት ግን በብዛት ሴቶች ላይ ይታያል።
  • ለብጉር መከሰት አራት መሰረታዊ ሁኔታዎች ምክንያት ናቸው

1- Follicular hyperkeratinization; ይህም የሞቱ ህዋሳት ተጠራቅመው የወዝ መተላለፊያ ቱቦ እንዲዘጋ ያደርጋል

2-የወዝ በብዛት መመረት (increased sebum production)

3-Propionibacterium acne የሚባለው የባክቴሪያ አይነት

4-ብግነት (Inflammation)

ብጉርን እና ብጉር መሰል ሽፍታዎችን (Acneiform eruption) የሚያባብሱ ነገሮች

ጭንቀት (stress)

ከመጠን ያለፈ ውፍረት

በወር አበባ አካባቢ

የሚዋጡም ሆነ የሚቀቡ መድሀኒቶች (steroids, phenytoin…)

በስራ ሁኔታ የሚያጋጥሙ ኬሚካሎች

በቆዳችን ላይ በሚከሰተ መፈጋፈግ (friction) ወይም ጫና (pressure) ፤ ለምሳሌ በህመም ሆነ በሌላ ምክንያት ለረጅም ግዜ በጀርባው የሚተኛ ሰው ጀርባው ላይ ብጉር ሊወጣ ይችላል ወይም የጡት ማስያዣ ገመድ የሚያርፍባቸው ቦታዎች ላይ ሊወጣ ይችላል

👉 ለረዥም ሰአት የፊት ማስክ ማድረግ

በውስጣቸው comedogenic ingredients የያዙ የፊትና የጸጉር ቅባቶች

ብጉር እንዴት ይታከማል?

ብጉር በአብዛኛው ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የቆዳ ህመም በመሆኑ በራሱ የሚጠፋውም ከእድሜ ጋር ተያይዞ ነው ፤ ስለዚህም ምልክቶቹን መቆጣጠር እንጅ በህክምና ማዳን (በአንድ ህክምና እስከ መጨረሻው እንዳይመጣ ማድረግ) አይቻልም።

በዚህም ምክንያት የብጉር ህክምና ወራትን የሚፈጅ በመሆኑ ታካሚዎች ከቆዳ ሐኪማቸው ጋር እየተመካከሩ ህክምናውን መከታተል ይኖርባቸዋል።

እዚህ ጋር ብጉር በራሱ ጊዜውን ጠብቆ የሚጠፋ ከሆን መታከም ለምን ያስፈልጋል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ፤ብጉር ከሚያሳድረው የስነ-ልቦና ጫና በተጨማሪ ሳይታከም በቆየ ቁጥር ፊታችን ላይ ጠባሳ የመፍጠር እድሉ የሰፋ ስለሆነ በጊዜ መታከሙ ይመከራል።

የብጉር ህክምና እንደ ጥንካሬው መጠን በሚቀባ ፣ በሚቀባና በሚዋጥ ወይም በሚዋጥ መድሀኒት ሊታከም ይችላል

See also  "እቤት ድረስ መጥተው እንጀራ አምጣ አሉት፤ እንጀራ ከቤቱ ይዞ ቢወጣም ገደሉት"

ከዋናው ህክምና በተጨማሪ በውስጣቸው Salicylic acid, Benzyle peroxide የያዙ መታጠቢያ ሳሙናዎች መጠቀም ያስፈልጋል

ከህክምናው በተጨማሪ ማድረግ የሚጠበቅብን

እንቅስቃሴ ማድረግ (ጭንቀት ለመቀነስ ይረዳል)

ብጉሮቹን ለማፍረጥ አለመሞከር (ጠባሳ እንዲፈጠር ስለሚያደርግ)

ለቆዳ ጤና መጠበቂያም ሆነ ለውበት የምንጠቀማቸው ምርቶች Oil-free & non-comedogenic መሆናቸውን ማረጋገጥ

ፀሐይ መከላከያ (sun-screen) መጠቀም (መጠቀም ያለብን የፀሐይ መከላከያ እንደ ቆዳችን አይነት ስለሚለያይ የቆዳ ሐኪም ያማክሩ)

ቆዳችን ላይ ጫና (pressure) የሚፈጥሩ ነገሮችን (helmets, ስልክ, የቦርሳ/የጡት ማስያዣ ገመድ, የፊት ማስክ) መቀነስ

ሰውነታችንን ካላበን መታጠብ

በመጨረሻም ከቆዳ ሐኪም ውጪ የተሰሩ ቪድዮችን አይተን ወይም የቆዳ ሐኪም ሳናማክር መድሀኒቶችን ገዝተን ባለመጠቀም ቆዳችንን ከተጨማሪ ጉዳት እንከላከል

ዶ/ር ዮሐንስ ታደሰ ፤ የቆዳና አባላዘር ህክምና ስፔሻሊስት

በሆሳዕና ከተማና አካባቢው የቆዳ ህክምናና ምክር ሲፈልጉ 0929296463

የሀኪም ቴሌግራምን ይጎብኙ: t.me/HakimEthio


Leave a Reply