በፔንሲዮን የተዘጋው የታሪኩ ህይወት፤ የሚስት ጭካኔ

ሰዎች በአጋጣሚ ተዋውቀው ትውውቃቸው ወደ ጠበቀ ግንኙነትና ባልንጀርነት ብዙ ጊዜ ያድጋል። በአጋጣሚ የተዋወቁ ሰዎችም በሚኖራቸው ግንኙነት እያደር አንዱ የአንዱን ማንነት፣ ባሕሪ፣ አመለካከት …ወዘተ ይበልጥ እየተረዳ ይሄዳል። በሂደትም ልብ ለልብ ሲግባቡ ወደ ፍቅር ሕይወት ይገባሉ። የፍቅር ሕይወታቸውም አብቦ ሶስት ጉልቻ የቀለሱ ብዙዎች ናቸው። በዚህ መልኩ ከመሰረቱ “ምን አላት? ምን አለው?” በሚል ቁሳዊ መስፈሪያ ሳይሆን በሰዋዊ መመዘኛ የተጀመረ ትውውቅ በመሆኑ የአብዛኞቹ ትዳር ሰምሮ ይስተዋላል። ልጅ ወልደው ለመሳም፤ ከምንም ተነስተው ሠርተው በሀብት ላይ ሀብት ለማፍራትም በቅተዋል።

ከላይ ለመንደርደሪያ ያህል እንዳነሳሁት በአንድ አጋጣሚ አቶ ምትኩ ተሰማ እና ወይዘሮ ገነት ግርማ ይተዋወቃሉ። በመካከላቸውም ይበልጥ የሚያቀራርባቸው አንድ ታላቅ ኃይል ተፈጠረ። ልባቸው አንዱ አንዱን በፍቅር ከጀለ። በልባቸው የተቀጣጠለው የፍቅር ኃይልም ከሐምሌ/2010 ዓ.ም ጀምሮ ትውውቃቸውን ወደ ፍቅር ግንኙነት አሳደገው። በፍቅር ግንኙነታቸው አስደሳች ምሽቶችንና ቀናቶችን ለወራት ያህል አሳለፉ። በፍቅር ሕይወታቸው ደስተኞች ነበሩ። ይህንን ደስታቸውን በአንድ ጣሪያ ስር ለማጣጣም በመወሰናቸው ከስድስት ወር የፍቅር ግንኙነት በኋላ ታኅሣሥ/2011 ዓ.ም ሶስት ጉልቻ ቀልሰው በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ላይ መኖር ጀመሩ።

በትዳር ዓለማቸውም በመደጋገፍና በመተሳሰብ ወራትን አስቆጠሩ። ከወራት በኋላ ይበልጥ ጋብቻቸውንና ፍቅራቸውን የሚያጸና ጽንስ ተፈጠረ። ይሄኔ ካለው የኑሮ ውድነት አኳያ ነገ ላይ ልጅ ሲመጣ የቤት ኪራይ ከፍሎ ቤተሰብ ማስተዳደር እንደሚከብድ ቀድሞ የተረዳው ምትኩ፤ የቤተሰቦቹ መኪና ላይ እንደረዳትና ገንዘብ ያዥ በመሆን ወደ ክፍለ ሀገር ዱራሜ ወደ ተባለ ከተማ በመሄድ ሥራ ይጀምራል። ይሁን እንጂ ባልና ሚስቱ በአካል ይራራቁ እንጂ በሃሳብ አንድ ነበሩ። ጠዋት ማታም በስልክ ይገናኛሉ።

ገነት የመውለጃ ቀኗ ሲደርስ ባለቤቷ ምትኩ ከአጠገቧ አልነበረም። ይሄኔ የቀድሞ ባለቤቷ አቶ ክፍሌ ሽጉጤ ከእርሷ ለወለዳቸው ልጆች መኖሪያ በተከራየው ቤት ውስጥ ህፃን ቃል ኪዳን ምትኩን ግንቦት/2012 ዓ.ም ወለደች። ባለቤቷ ምትኩ ከወለደች ከአንድ ወር በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ፤ ዓይኑን በዓይኑ ያሳየችውን ባለቤቱን ጠይቆ ልጁን ስሞ ከሁለት ቀን በኋላ ተመልሶ ወደ ሥራው ዱራሜ ያመራል። ከዚህ በኋላም በየጊዜው በስልክ እየደወለ ከመጠየቅ ባለፈ ለእመጫት የሚያስፈልገውን ከሰሉን፣ ዱቄቱን … ወዘተ እየያዘ ባለቤቱና ልጁን በየወሩ እየዘለቀ ይጠይቃቸዋል።

ነገር ግን ምትኩ ይህ በጎ ባሕሪው እያደር እየተቀየረ፤ ባለቤቱ ያልለመደችው አዲስ ባሕሪ ማሳየት ጀመረ። እሱም ባለቤቱ ገነት ስልክ ስትደውል አያነሳም። አንዳንዴ ደግሞ ከነጭራሹ ስልኩ ይዘጋባታል። ሚስት ያልለመደችው አዲስ ነገር ሲገጥማት “ለምን ስልክ ትዘጋለህ?” ብላ ባለቤቷን በስልክ ትጠይቀዋለች። ምትኩ በምላሹ “ዓመት ሊዘጋ ይችላል፤ መታገስ ነው ያለብሽ” ብሎ መልስ ይሰጣታል። እሷም መልሳ ስልክ ዘግታበት እንደማታውቅ ገልጻ፤ “ለምን ስልክህን ትዘጋለህ?” ብላ በድጋሚ ትጠይቀዋለች። ባልና ሚስቱ እንዲህ በስልክ አንድ ሁለት ሲመላለሱ በመሀል ምትኩ “አንቺ … እንትን፤ ሆቴል ለሆቴል እየዞርሽ ስሪ ፤ አንቺ … እንትን” በሚል የስድብ ናዳ በስልክና በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ያወርድባት ጀመር። ሚስትም በዚህ ቂም ትቋጥራለች።

ሆኖም “የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም” እንዲሉ ምትኩ ካፉ ያወጣውን በምንም ሊመልሰው ባይችልም፤ ባልና ሚስቱን የሚያስተሳስራቸው ፍቅርና ልጅ ስላላቸው ወደ አዲስ አበባ እየዘለቀ ሚስቱንና ልጁን መጠየቁን ግን አላቆመም። በየጊዜው እየዘለቀ ከባለቤቱ ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፎ፤ የልጁን ናፍቆት ተወጥቶ ወደ ሥራው ይመለሳል። ገነት የቀድሞ ባለቤቷ ለልጆቹ በተከራየው ቤት ስለምትኖር፤ ባለቤቷ ምትኩ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ልጃቸውን ይዛ ብዙ ጊዜ ተገናኝተው እየተጨዋወቱ የሚያድሩት በን/ስ/ላ/ክ ከተማ ወረዳ 02 ልዩ ቦታው ጀሞ ሚካኤል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ጎጆ ፔንሲዮን ነው። በዚህም የእንግዳ ማረፊያ ቤቱ ደንበኞች መሆናቸው ይታወቃል።

See also  የግብረ-ሶዶም ጥቃትና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈፀመው በ16 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

በጎጆ ፔንሲዮን ጣራ ስር

እንደ ወትሮው ሁሉ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 12:00 ሰዓት ገደማ ሲሆን ምትኩ ለባለቤቱ ገነት ደውሎ ከዱራሜ ወደ አዲስ አበባ እየመጣ እንደሆነ ይነግራታል። እሷም በጥቁር ቦርሳ የሷንና የልጇን ልብስ ከታ ልጇን አዝላ ቦርሳውን በእጇ አንጠልጥላ ወደ ጎጆ ፔንሲዮን አምርታ ሁለተኛ ፎቅ አልጋ ቁጥር ሁለትን ያዘች። አልጋውን ከያዘች በኋላ ከባለቤቷ ጋር “የት ደረስህ?” በሚል ሲደዋወሉ ጀሞ መስታወት ፋብሪካ አካባቢ እንደደረሰ ይነግራታል። እሷም ከዚህ ቀደም በሚገናኙበት የእንግዳ ማረፊያ ሁለተኛ ፎቅ አልጋ ቁጥር ሁለትን ይዛ እየጠበቀችው እንደሆነ ትነግረዋለች። ምትኩም ከደቂቃዎች በኋላ የተቀጣጠሩበት ቦታ ደረሰ። እንደደረሰ ገላውን ታጥቦ፣ ልብሱን ቀይሮ እራት ለመብላት ባልና ሚስቱ ተያይዘው ወጡ። እራት በልተው በጊዜ አልጋ ወደ ያዙበት ቤት ተመለሱ። በሰላም ሲጨዋወቱ አደሩ።

በነገታው ማለትም በ01/13/2013 ዓ.ም ባልና ሚስቱ አርፍደው 3:00 ሰዓት አካባቢ ከመኝታቸው ተነሱ። ፊታቸውን ታጥበው በፔንሲዮኑ አካባቢ ባለ አንድ ቁርስ ቤት ጎራ ብለው ቁርሳቸውን በልተው ዘወር ወር ካሉ በኋላ ወደ አደሩበት አልጋ ቤት ተመለሱ። በዚያም አደሩ፤ ዋሉ።

ባልና ሚስቱ ሁለት ቀን አብረው ካደሩ በኋላ በ02/13/2013 ዓ.ም፤ ምትኩ ወደ ሥራ ቦታው ዱራሜ ለማቅናት ጠዋት 12:00 ሰዓት “ሰላም ያገናኘን” ብሎ ወደ ዘነበወርቅ መናኸሪያ አመራ። ገነትም ያለ ባለቤቷ በአልጋ ቤቱ መቆየቱ አስጠልቷት እግር በእግር ተከታትላ በጠዋት ወጥታ ወደ መኖሪያ ቤቷ እያቀናች በተለምዶ ቻይና ካምፕ የተባለው አካባቢ ስትደርስ፤ ባለቤቷ ምትኩ ደውሎ “ለትራንስፖርት የሰጠሽኝ ብር ትንሽ ነው። ገንዘቡ ለትራንስፖርት ስላልበቃኝ መኪናው ሁሉ እየሞላ ሄደ። መጀመሪያ የሚበቃ ብር ሰጥተሽኝ ቢሆን አልጉላላም ነበር” በሚል ተበሳጭቶ ይደውልላታል።

እሱም አክሎ ከመናኸሪያ ወጥቶ መስታወት ፋብሪካ እንደደረሰ ገልጾላት፤ “ልምጣ ወይ?” ብሎ ይጠይቃታል። ሚስትም “ልምጣ” ሲላት እሷም ባሏን አክብራ ባለችበት ቁማ ጠበቀችው። እንደተገናኙም ተያይዘውም ወደ አደሩበት አልጋ ቤት ሄዱ። በዚያም ያደሩበትን አልጋ ቁጥር ሁለት ይዘው ቦርሳቸውን አስቀምጠው ክፍሉ እስኪ ጸዳ ድረስ ቁርስ ለመብላት ወጡ። ቁርስ ከበሉ በኋላ ምትኩ ጫት ገዝቶ አልጋ ወደ ያዙበት ቤት ተመልሰው ወደ ክፍላቸው ገቡ።

ምትኩም የተነጠፈውን የአልጋ ልብስ አንስቶ መሬት ላይ አንጥፎ፤ ባልና ሚስቱ መሬት ላይ ቁጭ ብለው እግራቸውን ዘርግተው አልጋውን በሽንጣቸው ወደ ኋላ ተደግፈው ጫት መቃም ጀመሩ። ሆኖም ገነት ከሁለት ቀን በፊት ባለቤቷ ወደ አዲስ አበባ እየመጣ እንደሆነ የነገራት ዕለት፤ ባለቤቷ ከዚህ ቀደም በስልክ ደውሎ በሰደባት ስድብ ቂም ይዛ ለመበቀል አስባ ከመኖሪያ ቤቷ ስትወጣ በጥቁር ቦርሳዋ የቡና መውቀጫ የብረት ዘነዘና ይዛ ወጥታ ኖሯል።

See also  ጨፌ ኦሮሚያ ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች እውቅና የሚሰጥ አዋጅ አጸደቀ

“ካሪያ እየተሳለ ጭድ ይበላል በሬ” እንዲሉ፤ ባልና ሚስቱ መሬት ላይ ቁጭ ብለው ጫታቸውን እየቃሙ እያወሩ እያለ፤ ምትኩ የባለቤቱ ስልክ ሲሙ ወጥቶባት እያስተካከለና ስልኩን እየነካካ ነበር። ገነት ባለቤቷ ሀሳቡ ስልኩን በመነካካት እንደተሰረቀ ስታውቅ ጫት ከምትቅምበት ቀስ ብላ ተነስታ ወደ ጥቁር ቦርሳዋ አመራች። በቦርሳዋ የያዘችውን የቡና መውቀጫ የብረት ዘነዘና አውጥታ ቀስ ብላ ባሏ ወደተቀመጠበት ተጠጋች። ዘነዘናውን በሁለት እጇ ይዛ ተንጠራርታ ባሏን ከተቀመጠበት ሳያስበው ከወደኋላ በኩል የኋላ ጭንቅላቱን ሁለት ጊዜ ስትመታው በተቀመጠበት ይወድቃል።

በወደቀበት በግራና በቀኝ ጆሮው አካባቢ ሁለት ጊዜ፣ ግንባሩ አካባቢ አንድ ጊዜ እንዲሁም መሀል አናቱ ላይ አንድ ጊዜ ደጋግማ ጉዳት ታደርስበታለች። ምትኩም በደረሰበት ጉዳት ደም አብሮት ከወደቀበት ተነስቶ እየተውገረገረ በር ሊከፍት ሲል ተሽቀዳድማ በሩን ከፍታ ወደ ውጭ ከወጣች በኋላ ተከታትሏት እንዳይወጣ በሩን ትዘጋበታለች። በረንዳ ላይ ቁማ እያየችው እያለ አዙሮት መልሶ ይወድቃል። ከዚያም በጭንቅላቱ ደም እያዘራ እንደምንም ተነስቶ በህፃኑ ማቀፊያ ፎጣ ጭንቅላቱን በመሸፈን በጀርባው ተንጋሎ አልጋው ላይ ይተኛል። እሷም አልጋ ላይ እራሱን ስቶ እንደወደቀ ስታውቅ ወደ ውስጥ ገብታ በሩን ዘጋች።

ይሄኔ የፔንሲዮኑ ባለቤት ወይዘሮ እመቤት ደርበው እና አልጋ አንጣፊዋ ወይዘሪት አበራሽ ተስፋ የጩኸት ድምጽ ሰምተው ባልና ሚስቱ አልጋ ወደ ያዙበት ክፍል ፊትና ኋላ ሁነው ያመራሉ። በዚያም ቀድማ አልጋ አንጣፊዋ ደርሳ በሩን አንኳኩታ “ምን ተፈጥሮ ነው? ምን ሆናቹህ ነው?” በሚል ይጠይቃሉ። ገነት በምላሹ “ከክፍለ ሀገር ተደውሎ የባለቤቷ ምትኩ አባት አርፈው” ተብሎ ባለቤቷ እያለቀሰ እንደሆነ ትነግራቸዋለች። ይህን መልስ ስትሰጣቸው የፔንሲዮኑ ባለቤትና አልጋ አንጣፊዋ “የክፍለ ሀገር ሰው መርዶ የሚያረዳበት የራሱ የሆነ ባህል አለው፤ ቀጥታ ደውሎ አባትህ አርፏል” ብሎ አያረዳም። ስለዚህ “አንድ የተደበቀ ነገር አለ” ብለው ባልና ሚስቱ ከያዙት አልጋ ጎን አልጋ ቁጥር ሦስት ውስጥ ገብተው አልጋ ላይ ቁጭ ብለው ሁኔታውን መከታተል ጀመሩ። የእንግዳ ማረፊያው ባለቤት ወይዘሮ እመቤት ሁኔታው ስላላማራቸው ከትንሽ ደቂቃ በኋላ ባልና ሚስቱ የያዙትን ክፍል መልሳ አንኳኩታ ምን እንደተፈጠረ እንድትጠይቃቸው አልጋ አንጣፊዋን ላከቻት።

አልጋ አንጣፊዋ አበራሽ በድጋሚ አንኳኩታ “ምን ሆናቹህ ነው? ተጣልታቹህ ነው?” ብላ ገነትን ጠየቀቻት። ገነትም “አዎ ተጣልተን ነው። በቃ ፖሊስ ጥሩ” ስትላቸው አልጋ አንጣፊዋና የድርጅቱ ባለቤት ቀድመዋት ወደ ምድር ቤት ወርደው ለፖሊስ ደወሉ። ተጠርጣሪዋም እግር በእግር ተከታትላ ባልና ሚስቱ ከነበሩበት የአልጋ ክፍል ልጇን አዝላ ቦርሳዋን በአንድ እጆ አንጠልጥላ ከሁለተኛ ፎቅ ወደ ምድር ቤት ወረደች። ተጠርጣሪዋ ከግቢ ሳትወጣ እና ተጎጂው በጣም ደም ፈሶት አልጋው ላይ በጀርባው ተንጋሎ ወድቆ እያንቋረረ ነፍሱ ሳትወጣ ፖሊሶች ይደርሳሉ። ፖሊሶቹም ደሙ እንዳይነካቸው በፌስታል እጃቸውን አስረው አልጋው ላይ ከወደቀበት አንስተው በፖሊስ መኪና ወደ ን/ስ/ላ/ክ ከተማ ወረዳ 02 ጤና ጣቢያ ይወስዱታል። ጤና ጣቢያ ከአቅማችን በላይ ነው ሲሉ ፖሊሶችም የተጎጂውን ሕይወት ለማትረፍ አንጠልጥለው ወደ አለርት ሆስፒታል ይዘውት ይሄዳሉ። በዚያም በሩ ላይ እንደደረሰ ገና ከሀኪሞች እጅ ሳይደርስ ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ላይ ምትኩ ሕይወቱ አለፈ።

See also  የሿሿ ማጅራት መቺዎችና የመሰረተ ልማት ዘራፊ ተጠርጣሪዎች ተያዙ

የገዳይ ቃል

ተጠርጣሪ ገነት ግርማ በፈጸመችው ወንጀል ተጸጽታ ፖሊስ ጥሩ ብላ እጇን ለፖሊስ እንደሰጠች ጠቁማ፤ ከላይ የወንጀል ታሪኩ በተገለጸው መሠረት ሟች ላይ ጉዳት እንዳደረሰች አምና፣ ነገር ግን ሕይወቱ ማለፉን የሰማችው ፖሊስ ጣቢያ እያለች ከሁለት ቀን በኋላ እንደሆነ ትናገራለች። ቀደም ሲል ሟች በስልክ ደውሎና በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ስለሰደባት ቂም ቋጥራ ስለነበር፤ በዚህ ቂም በቀል ተነሳስታ የወንጀል ድርጊቱን መፈጸሟን ለፖሊስ በሰጠችው የእምነት ክህደት ቃል ገልጻለች። ተጠርጣሪዋም ወንጀል የፈጸመችበት የብረት የቡና መውቀጫ ዘነዘና አልጋ ቁጥር ሁለት ከወደ ውስጥ በኩል ከበሩ ላይ ሰቅላ ማስቀመጧንና እንዴት የወንጀል ድርጊቱን እንደፈጸመች በቦታው ለፖሊስ መርታ አሳይታለች።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ወንጀሉ ከተፈፀመበት ቀን ማለትም ከ02/13/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተጠርጣሪዋን በቁጥጥር ሥር አውሎ፤ የተጠርጣሪዋን የእምነት ክህደት ቃል፣ የምስክሮችን የምስክርነት ቃል፣ የሟች አስከሬን የህክምና ውጤትና የአማሟት ሁኔታ የሚያሳይ ምስሎችና መረጃዎች አደራጅቶ ዐቃቢ ሕግ በተጠርጣሪዋ ላይ ክስ እንዲመሰርትባት መረጃውን አቅርቧል።

ዐቃቤ ሕግ

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539(1) (ሀ) ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሽ አደገኛና ነውረኛነቷን በሚያሳይ ሁኔታ ሰውን ለመግደል በማሰብ ከላይ በተጠቀሰው ቀን፣ ቦታ እና ጊዜ ባለቤቷ የሆነውን ሟች ምትኩ ተሰማን ከዚህ በፊት “እንትን …፣ እንትን …” እያለ ይሰድበኛል በሚል ቂም ይዛበት ቁጭ ባለበት አስቀድማ በቦርሳዋ ውስጥ ይዛው በነበረው የብረት የቡና መውቀጫ ዘነዘና የሟችን ጭንቅላት ስድስት ጊዜ ደጋግማ በመምታት ራሱ (ጭንቅላቱ) ላይ በደረሰበት ጉዳት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጋለች። በመሆኑም በፈጸመችው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አደራጅቶ በተከሳሽ ላይ ክስ መስርቶበታል።

 ውሳኔ

 ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሽ በ18 (በአሥራ ስምንት) ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።

 ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 20/2015


Leave a Reply