ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ውስጥ ሃያ በመቶው በካርታ አልተሸፈነም

ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ውስጥ 80 በመቶው በካርታ መሸፈን መቻሉን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።

የተቀረውን ቦታ በካርታ የመሸፈን ስራ በአንድ ዓመት ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጿል።

ካርታዎች በውስጣቸው ያለው የመረጃ ሀብት ለአየር ንብረት ትንበያ፣ ለመስኖና ተፋሰስ፣ ትምህርት፣ ለአሰሳና አቅጣጫን ለመለየት፣ ለሳይንስ፣ ለአደጋ ጊዜ ምላሽ፣ ለቱሪዝም፣ ለብሔራዊ ደህንነት፣ ለመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ለተፈጥሮ ሀብት አስተዳደርና ሌሎች መስኮች በግብአትነት ይውላሉ።

ካርታ ከሰዎች የስልጣኔ ዑደት ጋር ታሪካዊ ቁርኝት ያለውና መረጃዎችን በቀላሉና በምስል ማቅረብ የሚያስችል መሳሪያ ነው።

ኢትዮጵያ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ የቦታ መረጃ /ጂኦስፓሻል/ ስራ ታሪክ ያላት ሲሆን በዘርፉ ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል መልክአ ምድርን በካርታ ማንሳት ወይም መሸፈን ነው።

ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ የቆዳ ስፋት ያላት ሲሆን በአፍሪካ በቆዳ ስፋታቸው ቀዳሚ ከሆኑ አገራት 10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ፤ ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋት እስከ አሁን 80 በመቶው በካርታ መሸፈኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምትጠቀመው ካርታ አንድ 50 ሺኛ (1:50000) መስፈርት የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው እንደሆነም አመልክተዋል።

የተቀረውን ስፍራ በአንድ ዓመት ውስጥ በካርታ ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ቻይና የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋት 80 በመቶ የሚሸፍን የሁለት ሜትር “ሪዞሉሽን” (የምስል ጥራት) የሳተላይት መረጃ በነጻ ማቅረቧንና ይህም የካርታ መሸፈን ስራውን ለማሳለጥ ወሳኝ አበርክቶ እንዳለው ነው አቶ አብዲሳ ያስረዱት።

የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋት በካርታ የመሸፈን ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ያሉ ወቅታዊ ለውጦችን ታሳቢ ባደረጉ ማሻሻያ የማድረግ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ይህ ስራ ግለሰቦችና ተቋማት ስለ አንድ አካባቢ የተሟላና ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

የተለያዩ ተቋማትም ከካርታው የሚያገኙትን መረጃዎች በግብአትነት እየተጠቀሙበት እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የከተሞች የዲጂታል አድራሻ ስርዓት በተያዘው ዓመት ወደ ስራ እንደሚገባም ነው አቶ አብዲሳ ያስረዱት።

See also  የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ለዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ

ስርዓቱ ያስፈለገው መንገዶችን፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችና የተለያዩ ቦታዎችን በአቅጣጫ በመለየት የዲጂታል ቁጥር ተሰጥቷቸው እንዲታወቁ ለማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም ሰዎች ከተሞች ውስጥ ያሉ ቦታዎችን በመተግበሪያ በቀላሉ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መልኩ እንዲያገኙ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በቢሾፍቱ የዲጂታል አድራሻ ስርዓት የመዘርጋት ስራው ተጠናቆ በቀጣይ ወራት ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመው፤ በአዳማ ስርዓቱን የማበልጸግ ስራ 60 በመቶ መድረሱን ነው ያስረዱት።

በአዲስ አበባ፣ ደብረ ብርሃን፣ ባህርዳር፣ ጅማና ሃዋሳ ከተሞች በተያዘው ዓመት ስርዓቱን ወደ ስራ ለማስገባት እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝና በቀጣይ በሌሎች ከተሞች የማስፋት ሁኔታ እንደሚከናወን አብራርተዋል።

የዲጂታል አድራሻ ስርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ የሚገኝ አሰራር እንደሆነና በኢትዮጵያ ”ስማርት ከተሞች” ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

በአጠቃላይ የጂኦስፓሻል ስራዎች በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፉ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


Leave a Reply