መከላከያ ሰሰራዊት በእዩ ጩፋ ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑን አስታወቀ

የኢፌዲሪ የሀገር መከለከያ ሰራዊት በእዩ ጩፋ ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑን አስታወቀ።

በቅርቡ እዩ ጩፋ የተባለ ግለሰብ በሐይማኖት ስም እየተከተሉኝ ነው ያላቸውን ግለሰቦች ክብር ባልጠበቀ መልኩ ከነዩኒፎርማቸው በቪዲዮና ፎቶ ቀርፆ በአደባባይ እንዲሰራጭ አድርጓል።

ይህ የሰራዊቱን ስምና ታማኝነት በማሳጣት ለግል ፍላጎትና ጥቅም በማን አለብኝነትና ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን ለፈፀመው ድርጊት መከላከያ በህግ ለመጠየቅ መዘጋጀቱን የሰራዊቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ አስታውቀዋል።

ጥቂት የሰራዊታችን አባላትም ይህን ፍላጎት ለማሟላት የሁሉም ኢትዮጵያውያን መለያ የሆነውን ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ እንደነበሩ ተረጋግጧል ያሉት ኮሎኔሉ፤ ተሳታፊዎቹም በመከላከያ ወታደራዊ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ተይዘውና ታስረው ጉዳያቸውን ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የማጣራት ስራ እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።

በዚህ አይነት ጥፋት ከዚህ ቀደምም በተለያዩ የእምነት ተቋማት የተገኙ አባላት ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዶ እንደነበረ ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
ወደፊትም ፣ ማንኛውም የሰራዊት አባል የየትኛውም እምነት ተከታይ ቢሆን በእንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ ተሳትፎ ከተገኘ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል ።

የእምነት ተቋማትና መላው ህዝብ የመከላከያ ሰራዊቱን ዩኒፎርሙን ለብሶ በእምነት ተቋማት፣ በህዝቡ ዘንድ ነውር በተባሉ የመጠጥ ፣ የሱስ ፣ የቁማር ወዘተ ቦታዎች የሰራዊት አባልም ሆነ አስመሳይ ዩኒፎርም ለባሽ ሲመለከት እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል።

“ሰራዊታችን ፣ በጋብቻና በቀብር ጊዜ ፣ በእምነት ቦታዎች ክብሩን በጠበቀ መልኩ የሚከወኑ ስርዓቶች መኖራቸውና ሰራዊቱም እምነት ካለው ህዝብ የወጣ በመሆኑ ፣ በየግሉ ሐይማኖት ያለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በኛ በኩል በህጋችን የተፈቀዱና የተከለከሉ ጉዳዮችን በውስጣችን የማስረፅ ስራም ይሰራል” ብለዋል።
ኢ ፕ ድ

Leave a Reply