በሰሜን ወሎ ማህበራዊ ቀውሱ ከፍቷል፤ ትህነግ ሕዝብ አግቶ እያስራበና እያሰቃየ ነው

ከሰሜን ወሎ እየወጡ ያሉ መረጃዎች አስደንጋጭነት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው። የዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት አያሌው እንደሚሉት በዞኑ የተመዘገቡ ከ18 ሺ በላይ የስኳር ታካሚዎች፣ ከ20 ሺህ በላይ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎች፣ 1145 የቲቢ ታካሚዎች አሉ። እነዚህ የዕለት ተዕለት መድሃኒት፣ ሕክምና፣ ክትትልና ድጋፍ የሚያሻቸው ሰዎች እጣ ፈንታ አይታወቅም።

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አግቶ እያስራባቸውና እያሰቃያቸው ስለመሆኑ በግርድፍ ከሚሰማው በቀር ዝርዝር መረጃ ያለው አካላ የለም። ከሰሜንና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም ከአፋር እየተመታ የሸሸው ሃይል ሃይሉን በሰሜን ወሎ በዋግ ህምራ አጠናክሮ ህዝቡን ያገተበትን ምክንያት የሚቀርቡት ሚዲያዎች አልጠየቁትም፣ ድርጅቱም አላስታወቀም።

መውረር ብቻ ሳይሆን የጠላ ቂጣ “ኡንኩቶ” ሳይቀር እየዘረፈ እንደበላባቸው የሚናገሩ፣ ሊጥ እየዘረፈ እንደሚወስድ፣ ከተማ እንደሚያወድምና መሰረተ ልማት ከጥቅም ውጭ በማድረግና ሙሉ ዘረፋ ላይ እንደተሰማራ መረጃ እየወጣበት ያለው ትህነግ ለምን ከተማ እንደሚያወድም፣ንጽሃንን እንደሚጨፈጭፍ፣ የንጽሃኑ ጥፋትና በድለ ምን እንደሆነ በይፋ አስታውቆ አያውቅም። ሊያስተባብለው በማይችል መልኩ በመረጃና በማስረጃ የፈጸማቸው ግፎችና በደሎች አደባባይ ላይ ቢውሉም ዓለም በግልጽ ሲቃወመው አይሰማም።

ለዚህ ይመስላል ” ለውደፊቱ መነጋገር የሚቻልበት አግባብ እንኳን ቢኖር እንጥፍጣፊ አስቀሩ” በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃ እየወጣ ያለው።

ቢቢሲ ያናገራቸው ሃላፊዋ በእሳቸው ዙሪያ ያለውም መረጃ ሰጡ እንጂ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ክልሉ ያልሆነውንና ” ነጻ አውጣን” ብሎ ያልጠየቀውን ሕዝብና ስፍራ የሰው ማዕበል አሰማርቶ ከወረረ በሁዋላ የአካባቢውን የግንኙነት መሰረተ ልማት ስለሚያወድም በትክክል ምን እየሆነ እንደሆነ አይታወቅም።

በአብዛኛው ይዟቸው ከነበረበት አካባቢዎች በአብዛኛው ለቆ መውጣቱ ይታወቃል። ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ሕዝብ እየሰጠ ያለው ምስክርነት የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ስሜት እያስቆጣ ነው። አብዛኞች እንደሚሉት ቡድኑ ከሰሜን ወሎ ሲወጣ በተመሳሳይ የውድመት፣ ዝርፊያና የግፍ ዜና የሚጠበቅ ነው። በዚህ መካከል እጅግ አስጨናቂ የሆነው በአካባቢው የምግብ ችግር መኖሩና ምንም ዓይነት አገልግሎት ስለሌለ እየተሰማ ያለው የስቃይ ዜና እየከፋ መምጣቱ ነው።

የወልዲያ ከተማ ነዋሪ የነበረውና አሁን ተፈናቅሎ ደሴ ከተማ የሚገኘው ቴዎድሮስ ወልዲያ ስለሚኖሩ ቤተሰቦቹ ወሬ ከሰማ ከአንድ ወር በላይ የተናገረው ለቢቢሲ አማርኛው ዘግጅት ክፍል ነው። መጀመሪያ አካባቢ ከእርሱ በኋላ ተፈናቅለው ከሚመጡ ግለሰቦች ስለሁኔታው መረጃ ይሰማ ነበር። አሁን ግን ይህንንም ከሰማ ሳምንታት እንዳለፉት ተናግሯል።

ቴዎድሮስ እንደሚለው ከኑሮ ውድነቱና ከምግብ አቅርቦት እጦቱ ባሻገር የጤና አገልግሎት ባለመኖሩ የደም ግፊት፣ የስኳር፣ የኤችአይቪ፣ የቲቢ እና ሌላ ህመም የሚከታተሉ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል።

የሠሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት አያሌው በዞኑ ከ18 ሺ በላይ የስኳር ታካሚዎች፣ ከ20 ሺህ በላይ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎች፣ 1145 የቲቢ ታካሚዎች እንደነበሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አማጺያኑ “ወጣቶችን ወደ ጦርነት ይማግዳሉ” በሚል ስጋት እርሱ ቀድሞ ከአካባቢው መውጣቱን የሚናገረው ቴዎድሮስ ቤተሰቦቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሆኑ እንደማያውቅ ገልጿል።

“ስለ እነርሱ ሳስብ ነው የምውለው፤ የማድረው፤ ምን በልተው ይሆን? እንዴት ሆነው ይሆን? እያልኩ እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር የሚነጋበት ጊዜ ብዙ ነው” ብሏል።

ቴዎድሮስ እንደሚለው በእድሜ የገፉ እናትና አባቱ ከታናናሽ እህቶቹ ጋር እዚያው ወልዲያ ውስጥ መሆናቸውና አሁን ስላሉበት ሁኔታ አለማወቁ ይበልጥ አስጨንቆታል።

በሠሜን ወሎ ገጠራማ አካባቢ እናቷ እንደሚኖሩ የምትገልፀው ሌላኛዋ ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገች የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ደግሞ እናቷን በስልክ ካገኘች ሁለተኛ ወሯን መያዟን ትናገራለች።

እርሷ እንደምትለው ለወትሮው ብቻዋን የምትኖረውን እናቷን ውሎ ጠንቅቃ የማወቅ ልምድ ነበራት። አሁን ግን ያ የለም። ‘እንዴት ሆና ይሆን?’ የሚለው ሃሳብ ሰቅዞ ይዟታል።

“እናቴ ቁጡ፣ ፊት ለፊት የምትናገር፣ ብቻዋን የምትኖርበት ግቢ ውስጥ ያለ ፈቃዷ ወፍ ዝር የማታስብል፤ በሌላኛው ጽንፍ ደግሞ ለአንድ እንግዳ ሦስት እንጀራ ከሚገርም ጠላዋ ጋር የምታቀርብ ሴት ናት” ስትል የገለጸቻቸው እናቷ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አለማወቋ አሳስቧታል። ጦርነቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያልነካው ሰው የለም የምትለው የባሕር ዳር ነዋሪዋ፤ ጦርነቱ አብቅቶ የእናቷን ድምጽ እንደምትሰማ ተስፋ አድርጋለች።

ይህ በአንዲህ እንዳለ ትናንት ማክሰኞ በደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች በምግብና መድኃኒት እጥረት ለሚሰቃዩ ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ አደባባይ በመውጣት ጠይቀዋል።

ሰላማዊ ሠልፈኞቹ ‘ትኩረት በሰሜን ወሎ ለሚገኙ ወገኖቻችን’፣ ‘ወሎ መጠበቅ አይችልም!’ ‘ወሎ እየተራበ ነው!’ ‘ፍትሕ በምግብና መድሃኒት እጥረት ለሚሰቃየው የሰሜን ወሎ ሕዝብ’ የሚሉና ሌሎች መልዕክቶችን ማስተላለፋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ምስል ቢቢሲ – ከማህበራዊ ገጽ የተወሰደ

Leave a Reply