የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በትምህርት ስርዓት ውስጥ ሊካተት ነው

የትምህርት ሚኒስቴርና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ለማካተትና ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ተፈራርመዋል።

የስምምነት ሰነዱ የሰብዓዊ መብቶችን ወደ ማህበረሰቡ ከማስረፅ አኳያ ተደራሽነትን በመጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ተብሏል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሰላም ሊመጣ የሚችለው ሰብዓዊ መብቶች ሲከበሩ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም መብትና ግዴታውን መለየት የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በዚህም ረገድ ስምምነቱ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትና ስልጠና ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ለመሥጠት እንደሚሠራ በስምምነቱ ተገልጿል ።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትን በመደበኛው ትምህርት እንደ ግብረ- ገብ እና ዜግነት ትምህርት ውስጥ ትርጉም ባለው መልኩ በማካተት እንዲሠጥ ይደረጋል ተብሏል።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ስምምነቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን ከማስፋፋት አንጻር ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

“የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለሀገራችን ፈተና ሆኖ ቆይቷል ያሉት ኮሚሽነሩ ይህንንም ለመግታት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የምንሰራው ስራ ወሳኝ ነው” ብለዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም የሙያ እገዛ ከመሥጠት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚደረጉ መገለጹን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። Via OBN

See also  የመረጃና ደህንነት አገለግሎት አርማ ያለባቸው የዋሌት ምርቶች ለማጭበረበሪያነት እየዋሉ ነው፤ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

Leave a Reply