ይህ ኢስካንደር የሚባለው የኑክሌር አረር ቨተሸካሚ ሚሳኤል እስከ 500 ኪሜ ይጓዛል

ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ቤላሩስ ውስጥ ልታጠምድ ነው

ሩሲያ ስልታዊ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን በአጋሯ እና በጎረቤቷ ቤላሩስ ውስጥ በማንኛው ጊዜ እንዲተኮሱ ለማድረግ እንደምታጠምድ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ።

ፕሬዝዳንት ፑቲን አሜሪካ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን በአውሮፓ አገራት ውስጥ ማሰማራቷን በመጥቀስ፣ ይህ የሩሲያ ውሳኔ የኑክሌር ጦር መሳሪያን ለሌላ አገር ላለማስተላለፍ የተደረሰውን ስምምነት የሚጥስ አይደለም ማለታቸውን የሩሲያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ሩሲያ ስልታዊዎቹን የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ቤላሩስ ውስጥ ታሰማራ እንጂ፣ በእራሷ ቁጥጥር ስር እንደሚሆኑ ተናግረዋል። ይህ የሩሲያ ውሳኔ ይፋ ከሆነ በኋላ፣ አሜሪካ ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተዘጋጀች ነው ብላ እንደማታምን ገልጻለች።

የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ “ያሉንን ስልታዊ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን አቀማመጥ ለማስተካከል የሚያስገድደን ምንም ምክንያት አይታየንም” ብሏል።

ጨምሮም “ለኔቶ የጋራ የመከላከያ ስምምነት ያለን ተገዢነት ባለበት ይቀጥላል” በማለት ማንኛውም ውሳኔ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን አገሮች ጋር የሚወሰን መሆኑንም አመልክቷል። የጦር መሳሪያዎቹ የሚጠመዱባት የቤላሩስ መንግሥት ጠንካራ የሩሲያ ወዳጅ ሲሆን፣ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውንም ወረራ ይደግፈዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ቅዳሜ ዕለት በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሩሲያ አገራቸው ውስጥ ስልታዊ ኑክሌር መሳሪያዎችን እንድታሰማራ ሲጠይቁ እንደነበር ገልጸዋል።

ይህ የሩሲያ ውሳኔ የተለየ እንዳልሆነ የጠቀሱት ፑቲን “አሜሪካኖች ተመሳሳይ ነገር ለአስርት ዓመታት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ስልታዊ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቻቸውን ከረጅም ጊዜ በፊት ነው በወዳጆቻቸው አገራት ግዛት ውስጥ ያሰማሩት” ብለዋል።

ለእነዚህ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ማከማቻ የሚውሉ ቦታዎችን በመጪው ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ሩሲያ ገንብታ እንደምታጠናቅቅም ፑቲን ተናግረዋል።

ከወዲሁም የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን ማስወንጨፍ የሚችሉ ኢስካንደር የተባሉ ሚሳኤሎች ወደ ቤላሩስ መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

በዚህ የሩሲያ እርምጃ ከ30 ዓመታት ወዲህ ሩሲያ ከግዛቷ ውጪ የኑክሌር የጦር መሳሪያ ማስወንጨፊያ ማዕከል ሲኖራት የመጀመሪያው ይሆናል ተብሏል።

ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ሶቪየት ኅብረት ስትፈርስ የነበሯት የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ነጻ አገራት በሆኑት በሩሲያ፣ በዩክሬን፣ በቤላሩስ እና በካዛክስታን ውስጥ ነበሩ። ነገር ግን ሁሉም የኑክሌር አረሮች ወደ ሩሲያ እንዲመለሱ ተደርጓል።

See also  ʺዓለምን ናቋት በዝምታም ቀጧት"

ይህ የፑቲን ውሳኔ ይፋ የሆነው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከሩሲያ ጋር ለሚያካሂዱት ጦርነት ምዕራባውያን አጋሮቻቸው ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።

ከቀናት በፊት 18 የሚሆኑ አገራት በጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ዩክሬን በአንድ ዓመት ውስጥ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን የመድፍ ተተጓሽ ለመስጠት ስምምነት ፈርመዋል።

የመሳሪያ እና የተተኳሾች እጥረት የገጠማት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከአንድ የጃፓን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ሠራዊታቸው ተጨማሪ ተተኳሾችን እስኪያገኝ ድረስ በምሥራቅ በኩል ጉልህ ጥቃት ለመክፈት አይችልም ሲሉ ተናገረዋል።

ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው

Leave a Reply