በመራብ ክርስቶስን ማየትና ገነት መግባት ይቻላል ብሎ የሰበከው ፓስተር ተያዘ፣ 47 ሰዎች ሞተዋል

በኬንያ ምስራቃዊ ክፍል ማሊንዲ በተሰኘችው ከተማ “ከተራባችሁ ከኢየሱስ ጋር ትገናኛላችሁ፤ ገነትም ትገባላችሁ” የሚል አስተምሮ ይዞ የመጣ ፓስተር የ47 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።በዚህ ድርጊቱ በፖሊስ ተይዟል።

በጫካ ውስጥ ተደብቀው ራሳቸውን ከምግብና ከውሃ አርቀው የተባሉትን ሲጠባበቁ የነበሩና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ፍለጋውም ቀጥሎ ትናንት የ26ቱ አስከሬን ተገኝቷል።

ከዚህ ቀደም የ21 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን የሚያስታውሰው የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ፥ ይህም አጠቃላይ በዚሁ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ቁጥር 47 ያደርሰዋል ብሏል።

የማሊንዲ ከተማ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ሃላፊው ቻርለስ ካማኡ ግን ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችልና ፍለጋና ቁፋሮው መቀጠሉን ገልጸዋል። ከሞቱት ባሻገርም በጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ በመራብ ውስጥ ፈጣሪያቸውን ለመመልከት የሚጠባበቁ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በርካታ የሰው ሃይል አሰማርተን እየፈለግን ነው ብለዋል።

325 ሄክታር የሚሸፍነው ሻካሆላ የተሰኘው ጫካን እጅግ ሰፊ መሆኑ ግን የፍለጋ ስራውን ረጅም እንደሚያደርገው ነው የሚጠበቀው። የኬንያ ፖሊስ የዚህን ሁሉ ችግር ምንጭ የ“ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ቸርች” መስራች ፓስተር ማኬንዚ ንቴንጌ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገበት እንደሚገኝ ተገልጿል።

ፓስተሩ ባለፈው ወርም በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረ ቢሆንም በ100 ሺህ የኬንያ ሽልንግ ወይም 700 ዶላር ዋስ መለቀቁን የአካባቢውን መገናኛ ብዙሃን ጠቅሶ ፍራንስ24 ዘግቧል።
ንቴንጌ ከስድስት ተከታዮቹ ጋር በድጋሚ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራው ስለመጀመሩም ነው ዘገባው ያከለው።

የመብት ተሟጋቾች አሁንም የፓስተሩን አስተምሮ የሚከተሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንና መንግስት በጫካ ውስጥ የተደበቁትን ፈጥኖ ደርሶ ካልታደጋቸው ህይወታቸውን የሚያጡት ቁጥር ሊያሳቅብ እንደሚችል ገልጸዋል።

የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ኪቱሪ ኪንዲኪ በበኩላቸው፥ በቂ የጸጥታ ሃይሎች ወደ “ሻካሆላ” ጫካ መላካቸውንና ፍለጋውም ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

በነገው እለትም “የሞት ጫካ” ሲሉ ወደገለጹት አካባቢ እንደሚያመሩ ነው ያነሱት።
የሃይማኖት ነጻነትን እንደሽፋን በመጠቀም በአሳሳች አስተምህሮ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት የሚነጥቁ አካላት “የከፋ ቅጣት” ይጠብቃቸዋልም ብለዋል።

ምንጭ:— አል ዓይን አማርኛ

See also  በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር - የዓለምፀሐይ መኮንን

Leave a Reply