ይቅርታ የማያውቀው የፍረጃ መንደር አየር መንገድ ላይ የከፈተው ዘመቻ “ቅጥፈት ነው” ተባለ

ነዋሪነታቸውን አሜሪካ ያደረጉት ዶክተር ዮናስ ብሩ ነበሩ ቀድመው መንግስት የኢትዮጵያን አየር መንገድ ካርጎና ሎጂስቲክ ለቻይና በሽያጭ ሊያስተላልፍ ወይም በበድር ማስያዣነት ሊጠቀመው ነው በሚል የሚታወቅ መረጃ ሳያቀርቡ የተናገሩት። እሳቸው ይህን ማለታቸውን ተከትሎ ዜናውን በቅብብሎሽ ” አየር መንገድ ሊሸጥ ነው” ከሚል ትንታኔ ጋር አየር ላይ ተበተነ።

ለወትሮው ማጥራትና የመረጃን ምንጭ የማጣራት ወግ ያጣው የኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያ ለማንበብባ ለመስማት እንኳን ጊዜ ሳይወስድ በጥድፊያ ወሬውን አጨሰው። ” ማፈሪያ መንግስት፣ የጉድ አገር…” የሚል ተቀጽላ እየተጨመረ አየር መንገድ በዶክተር ዮናስ ብሩ አሳብ አመንጪነት፣ በተንታኞች ምኞት የአራጣ ማስያዣ ሆነ፣ ተሸጠ። ይህን ያሉ ሁሉ ዛሬ አየር መንገዱ እውነቱን ሲገልጽ አላስተባበሉም። ይቅርታ አልጠየቁም።

አገሪቱን እየመራ ያለውን መንግስት ለመቃወም በሚል በየቀኑ የኢትዮጵያ ምርጥ ተቋማት በመምረጥ ማጠልሸት፣ ለፕሮፓጋንዳ ሲባል የአገሪቱን ነባርና ገናና ተቋማት ማቆሸሽ፣ ህዝብን ቁጣ ውስጥ ለመክተትና ለአመጻ ለማነሳሳት የአገሪቷን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ማጉደፍ እጅግ የተለመደና ” ጀግና፣ አይበገሬ፣ አይተኬ፣የቁርጥ ቀን ልጅ…” ወዘተ እየተባለ የሚያስወድስ መሆኑ ሲታይ ደግሞ ” በውል የማይታወቀውና አገሪቱን እንዳሻው በትርምስ ውስጥ ሊነዳት የሚሞክረው አካል ምን አይነት ኢትዮጵያን ሊፈጥር እንዳሰበ አይገባንም” የሚሉትን ወገኖች ያስታውሳል።

ሰሞኑ አቶ ግርማ ዋቄ ከአየር መንገድ ቦርድ ሰብሳቢነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ እሳቸው ሳይጠየቁ ሲናፈስ የነበረው ወሬ ቢያንስ አቶ ግርማ ” ስንት ዓመታቸው ነው? ዕረፍት አያስፈልጋቸውም? እስከመቼ ምርታማ ሆነው ይሰራሉ…? የሚል ጥያቄ ለማንሳት አልሞከረም። ይህ ብቻም አይደለም ምርጡ ባለሙያ አቶ ግርማ ራሳቸውን ችለው መግለጫ መስጠትና መናገር የሚችሉ ስለሆኑ ለምን አይጠየቁም? ካለፈም በሁዋላ ተጠይቀው በተነዛው ወሬ ደረጃ ችግር እንዳጋጠማቸው ይፋ አላደረጉም። የአስተዳደር እይታ የአሳብ አንድነት አለመኖሩ ቢገለጽም የአየር መንገዱን ስም በሚያጠለሽ ደረጃ ያሉት ነገር አልተሰማም።

በውል በማይታወቅ መረጃና የዘመቻ ፕሮፓጋንዳ እሳቸውን ተኩ የተባሉት ጀነራል ይልማ መርዳሳን የመሰለ ጀግና ማዋረድን ምን አመጣው? የኢትዮጵያን አየር ሃይል አመድ አራግፎ፣ አረም መንጥሮ፣ ርዝራዡን አጽድቶ ለከፍተኛ ደረጃ ያበቃ ጀግናን መስደብና ማዋረድስ እንዴት ሆኖ ሰዳቢውን ቧልተኛ ” ጀግናችን፣ አንተ ባትኖር?” የሚል ሙገሳ ያሰጠዋል? ሹመቱ አግባብ አይደለም አከተባለ በጨዋነት በአዋቂዎችና በመረጃ መተቸት ሲገባ በዚህ ደረጃ የአገር ጀግኖችን ማራከስ እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ ህሊናቸውን የሚገዙ ኮንነውታል።

See also  ዓለም ጆሮ የነፈገው ዳግም እልቂት በትህነግ እየተፈጸመ ነው

ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመተቸትና ለመፈታተን በርካታ ምክንያቶች እያሉ በውሸትና በቅጥፈት መረጃዎች አየሩን የሚሞሉ “ተምረናል” የሚሉ ዜጎችን ማየት እንደ አገር አፍረት ሊሆን ሲገባ ” ጅግና” የሚያስብል መሆኑ፣ ” ኢትዮጵያ ልትፈርስ ቀናት ቀርተዋታል” የሚል የውድቀት አዋጅ ለማወጅ መነሻ ማዕረግ ሆኗል። ሰው ለአገሩ ውድቀትን ዕለት ዕለት ለማውጅና ዜጎችን በስጋት ማማቀቅ ” አይተኬ” የሚል ክብር ማሰጠቱ ብቻ ሳይሆን የሃሰተኛ መረጃ የስርጭት ፍጥነት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ነውና ነገሩ የሚቆም አይመስልም።

የህዳሴ ግድብ እንዲሸጥ አብይ አህመድ አዘዋል፣ መስቀል አደባባይ ሊፈርስ ነው፣ ወልቃይት ለትህነግ እንዲመለስ ተወሰነ፣ ደብረ ኤሊያስ ገዳም ነደደ፣ ፈረሰ… የሚሉ ዜናዎችን ሲረጩ የነበሩና ህዝብን ጥቁር አስለብሰው ለሞት ሲጋልቡት የሰነበቱ ዛሬ ደግሞ አየር መንገድን ተነስተውበታል። አየር መንገድ በድረ ገጹ ለቻይና ሊተላለፍ ወይም ሊሸጥ ነው በሚል አንድ የኢኮኖሚ ዶክተር፣ ታላላቅ ሃላፊነት ላይ የሰራ ሰው ያሰራጨውን የሃሰት ዜና እንደሚከተለው በጨዋነት ተቃውሟል።

“ድርጅታችን በጥቂት የማሕበራዊ መገናኛ ብዙሐን ላይ እየተናፈሰ ያለውን ‘የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት (ካርጎ እና ሎጂስቲክስ) ክፍል ወደሌላ ሀገር በሽያጭ ሊተላለፍ ወይም ለብድር መያዣነት ሊውል ነው’ የሚል የፈጠራ ዜና ተመልክቷል፡፡ ዜናው ፍጹም ከዕውነታ የራቀ እና መሰረተ-ቢስ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያረጋግጣል። ይህ ከእውነት የራቀ ወሬ የብሔራዊ አየር መንገዳችንን ስም እና ገፅታ የሚጎዳ ስለሆነ ወሬውን የሚያሰራጩ ወገኖቻችን ይህንን ከማድረግ እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን” ማንኛውንም የተሟላ መረጃ ለማግኘት ድረ ገፃችንን www.ethiopianairlines.com ይጎብኙ።

Leave a Reply