ሃቺኮ- የዓለማችን እጅግ ታማኙ ውሻ

“ምንም ያክል ጊዜ ይፍጅ እጠብቅሃለሁ”

ይህ አገላለጽ እውነተኛውን የሃቺኮ ታሪክ ያስታውሳል።

ሃቺኮ ውሻ ነው። ለባለቤቱ እጅግ ታማኝ የነበረ ውሻ።

ሃቺኮ አንድ ልማድ ነበረው። ባለቤቱን ባበሩር ጣቢያ ላይ ጠብቆ ከዛ ወደ ቤት አብሮ መሄድ። ባለቤቱ ድንገት ሕይወቱ አለፈ። ሃቺኮ ግን ሰውዬን ለዓመታት ባቡር ጣቢያ ጋር ቆሞ ጠብቆታል።

ይህ ውሻ የተወለደው የዛሬ 100 ዓመት ነበር። የውሻው ታሪክ በፊልም እና መጽሐፍ ሚሊዮኖች ጋር ደርሷል። ቶኪዮ በሚገኘው ባቡር ጣቢያም ሃውልት ተቀርጾለት የበርካታ ጎብኚዎች ቀልብን እንደሳበ ነው።

ጃፓናውያን ተማሪዎች በትምህር ቤቶች ውስጥ ታማኝነትን ከሃቺኮ ተማሩ ይባላሉ።

የሃቺኮ ታሪክ

አኪታ የተባለ የውሻ ዝርያ የሆነው ሃቺኮ የተወለደው በ1923 በጃፓኗ ከተማ ኦዳቴ ነበር።

ዝርያቸው አኪታ የሆኑ ውሾች የተረጋጉ፣ ብልህ፣ ደፋር እና ለባለቤቶቻቸው ታማኝ የሆኑ ውሾች መሆናቸው ይገለጻል።

ሂሴሳቡሮ ኡኤኖ የተባሉ አንድ የግብርና መምህር እና ውሻ አፍቃሪ ተማሪዎቻቸው የአኪታ ዝርያ የሆነ ቡችላ እንዲፈልጉላቸው ይጠይቃሉ።

ሃቺኮን አገኙ። ከረዠም የባቡር ጉዞ በኋላ ሃቺኮ ከመምህሩ መኖሪያ ቤት ይደርሳል።

ቡችላው ከመምህሩ ቤት ሲደርስ እጅግ ከመዳከሙ የተነሳ የሞተ መስሎ ነበር። መምህሩ እና ባለቤታቸው ሳይሰላቹ ለተከታታይ ስድስት ወራት ለቡችላው እንክብካቤ አድርገው የውሻው ጤና ተመለሰ።

መምህሩ ኡኤኖ ለአዲሱ ቡችላቸው ሃቺ (በጃፓንኛ ስምንት ማለት ነው) የሚል ስም ሰጡት። ‘ኮ’ የምትለው ቅጥያ በመምህሩ ተማሪዎች የተሰጠች ነች።

የሃቺኮ ሃውልት

ረዥሙ ጥበቃ

መምህር ኡኤኖ በሳምንት ለበርካታ ቀናት ወደ ሥራ የሚሄዱበት በባቡር ነበር። መምህሩ ቶኪዮ ከተማ ወደሚገኘው ሺቡያ ባቡር ጣቢያ ሲሄዱ ሁሌም በሦስቱ ውሾቻቸው ታጅበው ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዱ ሃቺኮ ነው። ውሾቹ የመምህሩ መመለሻ ሰዓት አመሸሻ ሲደርስ ወደ ባቡር ጣቢያው ሄደው ጌታቸውን ይጠብቃሉ።

ሃቺኮ ከመምህሩ ጋር ለ16 ወራት ከኖረ በኋላ መምህሩ ድንገት ጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ አጋጥሟቸው ሕይወታቸው ያልፋል።

የሃቺኮን ታሪክ ሰንደው ያስቀጠሙት ፕሮፌሰር ማዩሚ ኢቶሃ በለቅሶ ስነ-ስርዓት ወቅት ሃቺኮ የመምህሩን አስክሬን ከያዘው የሬሳ ሳጥን ስር ተኝቶ አልነሳም ስለማለቱ ጽፈዋል።

See also  አተራምሱና ማማ ላይ ... አይ አሜሪካ

ከመምህሩ ሞት በኋላ ሃቺኮ ለሌላ ቤተሰብ ተሰጠ። ከጥቂት ወራት በኋላ ግን ከመምህሩ ጋር ይኖር ወደነበረበት አካባቢ ይመለሳል።

በዚህ ወቅት ነበር የብዙዎችን ልብ የሰበረ ተግባር መፈጸም የጀመረው።

ሃቺኮ በየዕለቱ ዝናብም ሆነ ሃሩር ጸሃይ ሳያግደው ባለቤቱን ጥበቃ ወደ ባቡር ጣቢያው መመለስ የጀመረው።

ፕሮፌሰር ማዩሚ ኢቶሃ አመሸሻ ላይ ሰዎች ከባቡር መውረድ ሲጀምሩ አለቃውን ፍለጋ በአራት እግሮቹ ቆሞ ተጓዦችን አንድ በአንድ ይመለከት ነበር ይላሉ።

መጀመሪያ ላይ የባቡር ጣቢያው ሠራተኞች ውሻው ባለቤት አልባ የመንገድ ላይ ውሻ መስሏቸው ነበር። ልጆች ይመቱት ነበር። በአካባቢ የነበሩ ነጋዴዎች ደግሞ የውሻውን ታሪክ ሳያውቁ ውሃ እየደፉበት ለማበረር ይሞክሩ ነበር።

ሃቺኮ ግን ይህ ሁሉ ሳይበግረው በየዕለቱ እየተመለለሰ የማይመጡ ጌታውን ከባቡር ጣቢያ መጠበቁን ቀጠለ።

ሃቺኮ

ሃቺኮ እውቅና ያገኘው የጃፓኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ቶኪዮ አሳሂ ሺምቡን ስለውሻው በጥቅምት 1932 ከፃፈ በኋለ ነው።

ከዚያ በኋላ ጣቢያው ለሃቺኮ የሚሆን የምግብር እርዳታ ያገኘው ጀመር። ጎብኚዎችም ከሩቅ ቦታ ውሻውን ለማየት ይጎርፉ ጀመር።

ስለውሻው ሃቺኮ ግጥም የሚፅፉ በረከቱ። በ1934 ለውሻው የሚሆን ሃውልት ለመሥራት ገንዘብ መዋⶐ ተዘጋጅቶ 3 ሺህ ሰዎች ታደሙ።

ሃቺኮ መጋቢት 1935 ከዚህች ዓለም በሞት ተለየ። ጋዜጦች የሞቱን ዜና የፊት ገፃቸው ላይ ይዘውት ወጡ።

በቀብሩ ሥነ-ሥርዓት የተገኙ የቡድሃ እምነት መነኩሴዎች ፀሎት አደረጉ። የሕይወት ታሪኩ በረዥሙ ተነበበ።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሃውልቱን ለመጎብኘት ይጎርፉ ጀመር።

የሃቺኮ ሃውልት የሚገኝበት ሥፍራ እጅግ ታዋቂ ነው። ፖለቲካዊ ተቃውሞ የሚደረግበትም ሥፍራ ሆኗል።

ጃፓን ከጦርነት ከተላቀቀች በኋላ ለሃቺኮ አዲስ ሃውልት ለመሥራት መዋጮ ተደርጎ 800 ሺህ የን ተሰበሰበ። ይህ ገንዘብ ዘንድሮ ቢሆን 4 ቢሊዮን የን ያወጣል።

“መምህር ኡየኖ እንደማይመጣው ያውቀዋል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን መጠበቁን ቀጠለ። ይህ ስለእምነት ብዙ ያስተምረናል” ሲል ኦኮሞቶ ታኬሺ በ1982 ፅፏል።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ሃቺኮ አለቃውን ባቡር ጣቢያ ሲጠብቀው ተመልክቷል።

በየዓመቱ ሚያዚያ 8 ሃቺኮ ከሺቡያ ባቡር አጠገብ ይዘከራል።

See also  [የሽግግር መንግስት] ሊቋቋም ነው !!

ሃውልቱ አሸብርቆ ይታያል።

በቶኪዮ ብሔራዊ የተፈጥሮና ሳይንስ ሙዚየም ውስጥም ሃውልት አለው።

ቅሪቱ ከዩኤኖ እና ያየ ጋር አንድ ላይ ሆኖ በአዮዋማ መኻነ መቃብር ይገኛል።

ዘንድሮ መቶኛ ዓመቱን የሚያከብረው ሃቺኮ የተለያዩ መዘክሮች ተዘጋጅተውለታል።

ከቢቢሲ የተወሰደ

Leave a Reply