ጮማ እያየህ ቀበቶህን ብላ – ቪአይፒ ቁርጥ ቤቶች – የከርስ ፖለቲካ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተተከለው ከርስ ላይ ነው። ለከርሳቸው ሞተው የሚኖሩ!! ለክፋቱ ከርስ አድሮ ያው ነው። ትናንት በላሁ አያውቅም። ከርስ ላይ የተተከለው ፖለቲካችን ብዙ “ከርስ አደሮችን” ስላመረተ ከከርስ ፖለቲካ መውጣት ቀላል አይሆንም። የነጻ አውጪነት ፖለቲካ ራሱ የከርስ ፖለቲካ ነው። ቁማር ነው። ብር መሰብሰቢያ ነው። ህዝብ መማገጃ ሃሺሽ ነው። … የከርስ ፖለቲካ ከርስ ሲጎድል ያናጫል፣ ያባላል፣ ያጋድላል፣ ያለያያል። ያካክዳል። በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ፓርቲ ሲቋቋም፣ ሲባላ፣ ሲሰነጠቅ፣ ሲካካድ፣ ሲውነጃጀል የሚሰማው ሂደቱ ሁሉ “ከርስ ተኮር” በመሆኑ ነው። የከርስ ፖለቲካው ታዲያ ከውጭም ከውስጥም ነው። መነሻውም መድረሻውም ብር ነው። ፋይል አገላብጡ ….. ብር…. በርከት ሲል ጸብ … እያጋደሉ ፡ብዙ ዓይነት” ቁርጥ መቁረጥ … ቦሰና “ይድፋችሁ” ትላለች!!

ድንገት ስልኩ ጮኸ። ሁካታ ይሰማል። “ያለሁት ስጋ ቤት ነው። ቁርጥ ቤት። ጮማ ቤትና ቀበቶ ቤት። ቆዳ ቤት።…..” እያለ ደዋዩ … ” ጮማ ቤት ቀበቶ ቤት” ያበደው የሰማውን ባይኑ ካየው ጋር በፍጥነት አሳሳመና ወሬውን አሰላ። “ኢትዮጵያ ብልጽግናዋ በስጋ ቤት ይረጋገጣል” ሲል ያበደው መፈክር አሰማና ተስፈነጠረ።

እንደምን ከርማችኋል። ስንከሰት በተደጋጋሚ ነው። ጮማ ወሬ ሲገን ከች እንላለን። እንኳን ለ119ኛው ዓመት የአገር መከላከያ ቀን አደረሳችሁ። ያበደው ወፖን፣ ነበልባልን፣ ልዩ ኮማንዶን ሲያይ እምባው መጥቶ ነበር። ባህር ሃይል ዳግም ተውልዶ ነጭ ነዶውን ሲወዘውዝ ያበደው የሚሆነውን አሳጣው፤ አየር ሃይል አብቦ ፈክቷል። “የደርግ” ብለው የበሉት ጦር ዳግም ተሞሸረ። አይ ቀን፣ አይ ጊዜ፣ አይ … መከታዎቻችን ወግ አዩ። ኢትዮጵያ በወጉ አመስገነቻቸው … ይህኛው ጦር በአልቡባልታ …. ብቻ ይቅር …

አዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ ሲቀጥልም በየክልሉ ብዙ ዓይነት የቪአይ ፒ ወይም የልዩ እንግዶች መስተናገጃዎች አሉ። ያበደው የጨቅላ ሃጻናት “ማስገሻ” ዝግ ቤቶችንና የስጋ ቤት ቪአይፒዎችን አይቷል። የዛሬን አይድርገውና የውሽማ ቀን የሚከበርበትም ቦታ ነበር። ዛሬ አክባሪና አስከባሪዎቻቸው በግል ተከርችሞባቸዋል። ነፍዘዋል። አብረው ሲያልቡ ኖረው ተካሰዋል። ሌባና ቀማኛ ተባብለው አንዱ ሌላው ላይ ሪፕፖርት ለመጻፍ ፈርሰዋል። አይ ግፍ …. ሲጥል እንዲህ ነው። እድሜ ደጉ ብዙ ያሳያል። የባልደረቦቻቸውን ሚሽቶች የሚያማግጡባቸው ስውር ቤቶችም ያሉዋቸው ልክስክሶች አሉ። ሲያዩዋቸው ሰው የሚመስሉ ውርዴዎች ብዙ ናቸው። ኢትዮጵያ ብዙ አይነት ቶራ ቦራዎች አሉዋት። የአፍጋኒስታን ቶራ ቦራ፣ የሟቹ ቢንላደን መደበቂያ ከተማ ቶራ ቦራ እዚህ የሚሰራበት ሌላ ነው… የሙት ወዳጆቻቸውን ሚስትን ለሚያማግጡ፣ የዘረፉትን እየበተኑ ህጻናትን ለሚያበላሹ መዳሪያ፣ ከርስ መሙያው ልዩ ክፍል፣ ልዩ ሳሎን፣ ልዩ መስተንግዶ፣ ልዩ ክብር …. ብር ብር ብር …. የኔታ ነፍሳቸውን ይማረውና “ከሽፈናል” ብለው ነበር … “አልከሸፍንም” ሲሉ የተውተረተሩ መጣፍ ገላጮችን ያበደው ያስታውሳል…

አዲስ አበባ ዛሬ ህንጻዎቿ ሳይቀር የቁርጥ መቁረጫ ሆነዋል። የቁርጥ ቤት ገበያ ራሱን የቻለ ፖለቲካ ሆኗል። ቁርጥ ስለሚወዱ ብቻ አዳብለው፣ ያላቸውን አጋጭተው የሚሄዱ አሉ። ያበደው የሚያወራው የሰፈር ስጋ ቤቶችን ሳይሆን በውስጣቸው ልዩ ሳሎን አዘጋጅተው በዝግ ባለስልጣንና የባለስልጣን ቢዝነስ አመቻቾና ሃብታሞችን የሚያስተናግዱትን ቁርጥ ቤቶችና የሚፈጸመን መድልዎ ነው። ባለ ሳሎን ቤቶቹ ቁርጥ ቤቶች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማሳያ ናቸው።

እነዚህ ቁርጥ ቤቶች ” ጮማና ቀበቶ ” ለገበያ ያቀርባሉ። ስጋና ጠፍር እያቀረቡ መድልዎ ይሰራሉ። ቪአይፒ ስጋ እያማረጠ ይቆርጣል። ከፈለገም አኝኮ ተፍቶ ያስቀይራል። በተዘጋው ልዩ ሳሎን ውስጥ ሆነው ሰፊው ህዝብ ቆዳ “ሲቆርጥ” ያያሉ። ከዛ ወጥተው “ብልጽግናችን በደጃችን፣ ብልጽግናችን በጃችን” ሲሉ የኮንዶም አይነት ማስታወቂያ ያወርዳሉ። ይምላሉ። አይናቸውን በጨው ያጠቡ እንደሆኑ ቦሰና ዘወትር ትናገራለች።

See also  አተራምሱና ማማ ላይ ... አይ አሜሪካ

እንደ ቪ ላውንጅ አይነት ማጅራት መምቻ ቤቶች ለአንድ ጠረጰዛ አስር ሺሆችን መክፈል ቀላል ጨዋታ ነው። የብልጽግና ካድሬዎች እዛም አሉ። የብልጽግና ሹመኞች የተከላካይ ተጨዋቾችም አሉ። ቅምጥ ሚዲያዎችና የሚዲያ አዝማቾችም አሉ። ቪአይፒዎች ናቸው። ከውስጥም ከውጭም ጋርዶች አሉ። መጠጣት፣ መክፈል እንጂ ሰክሮ እንዳሻ መሆን አይቻልም። አንዱን ዲያስፖራ “ሰከርክ” ብለው በቦክስ መንጋጋውን ብለው ሲቆልፉት ያበደው አይቷል። ይህ መደበኛ አሰራር እንደሆእ ተነገሮታል። ሞቅ ሲላቸው በባለስልጣን ስም የሚምሉ፣ የሚናዘዙ፣ ሲያሻቸውም ደውለው በዛ ጩኸት ውስጥ መመሪያ የሚሰጡ እንዳሉ ያበደው አይቷል።… ብዙ ብዙ አሉ። አንዳንዴ ኢንተርቪው አድራጊና ተደራጊ አብረው ይታያሉ። ቀን በቲቪ አበልጽገው ማታ ከርሳቸውንና ስሜታቸውን ያበለጽጋሉ። ያበደው “ኮንዶም ሳትገዙ ሱቅ እንዳይዘጋ” ብሎ ተርቧል። … “ሰርታችሁ እንኳን ቢሆን የምትኮፈሱት” ሲሉ ጠቅላዩ “ሰው ሁኑ” ያሉዋቸው እዛ ሰፈር የሚልከሰከሱትን ላለመሆኑ ያበደው መረጃ የለውም ….

“ኤጭ” ትላለች ቦሰና። ቦሰና ሲመጣባት አንስታ መለጠፍ ነው። “እንደዚህ እየተልከሰከሱ ሚዲያ ላይ ሲቀርቡ …” ትልና “ነጠላዎች፣ የሰው …” ብላ ምለስ ትልና ” አንተ በስንቱ ትልቃቸዋለህ” ብላ ደጎልን ታመሰግነዋለች። ሱፍ ቢለብስ፣ ክራባት ቢያደርግ፣ ነጩን መኪና ቢነዳ … ብላ ትዘርዝርና … የምክትሉን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አይበልጠውም … “ስምህን ቄስ ይጥራው” ትላለች እንጂ ስሙን አታነሳውም። ብዙ መረጃ ስላላት ተሰው አትቆጥረውም። ጥቁር ለብሶ “ለሃይማኖቴ ለኦርቶዶክስ” ብሎ የለጠፈውም አይታ ” ለማያውቅህ” ስትል በድንግል ስም አታጭበርብር ብላዋላች …. ቦሰና ብዙ መረጃ አላት …

አንዴ ከዱከም እስከ ቢሺፍቱ ዝግ ቤቶች በድንገት ታሰሱ። በዝግ ቤቶች ውስጥ የተያዙት በሙሉ የወረዳና የዞን ባለስልጣኖች፣ መሃንዲሶችና ፖሊስ አመራሮች ሆኑ። ኢህአዴግ በስብሶ ሊገነደስ ጥቂት ሲቀረው ካድሬዎቹ ጫት ቤትና ሺሻ ቤት ሆነ ነበር የሚሰሩት። ያበደው ብዙ ውሳኔዎች ከጫት ቤት ሲወሰኑ ቀርጿል። በጫት ቤት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይበለታል። መመሪያ ይሰጣ። ኢህአዴግ የበስበሰው ጫት ቤትና በለበሰው “ኮት” ውስጥ ሆኖ ነው። ዛሬም ያ ላለመደገሙ ማረጋገጫ የለም። በስልክ በሚሊዮን በጀት እይስመደቡ የሚዘርፉ ከርሳም ካድሬዎች …..

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” ኮት ለብሰህ አትወጠር፣ ጓዶቻችን ኮት ለብሰው ሲወጠሩ ለካ ቀፎ ነበሩ .. ” ያሉት ለዚህ ይሆን? ያበደው ቆመ። ብዙ ዓመታት ወደ ሁዋላ ተመለሰ። አዋሳ የኢህአዴግ ጉባኤ ነበር። ልክ እረፍት ላይ ካድሬው ሁሉ ኮብራውን እያስነሳ በርጫ ሊመታ ወደ ሆቴሉና ወንዶ ሲከንፍ የአሁኑ ጠቅላይ ንጹህ ልብስ ለብሰው መጣፍ ያነቡ ነበር … ከምር !! ያበደው ከሁለት የክልል መሪዎች ማደሪያ የጫት ጋራባ በገፍ ሲጠረግና ሲወጣ አይቷል። የታችኞቹ ለጉድ ነው … ታከለ ኡማ ብቻ ነበሩ የማይቅሙ ከንቲባ … ይህ ምስክርነት እውነት ነው። ከጫት መልስ ጉባኤው ሲቀጥል በሚርቃና ከንፈራቸውን የሚላምጡ፤ ላብ የሚያርሳቸው … አቤት ….

የቪአይፒ ክፍሎች ባሉዋቸው ስጋ ቤቶች ውስጥ ተራ ተጠቃሚ ሆነው የሚሄዱ ቀበቶ ይበላሉ። ያው የማይታኘክ ከሆነ ከቀበቶ ምን ይለየዋል? ቦሰና “አኞ” ትላለች። የማይታኘክ ስጋ ብቻ ሳይሆን የማይጥማትን ሁሉ “አኞ ነገር” ትላለች። ካድሬ አትወድም። በተለይም የምታውቃቸው ሌቦች በሚዲያ ወጥተው ያልሆኑትን ለመሆን ሲጋጋጡ ትጠየፋቸዋለች። “አኞ ነገር” ብላ ትሳደባለች። ለካድሬ ሊሰጥ የሚገባውን አኞ ለትክክለኛው፣ ሰርቶ ባገኘው ሊበላ ለሚመጣ ደንበኛ ይሰጣሉ። ሰው እንዴት በንግድ ቤት ሰው ይመርጣል? ነጋዴ ቪአይፒ ብሎ በአደባባይ ቀማኛ ካድሬ በዝግ ይቀልባል?

See also  የሚዘጋባቸው ህጻናት – ዝግ ቤቶች

ቪአይፒ ክፍሎች ውስጥ ስጋ ብቻ ሳይሆን ውስኪ እንደ ጠጠር ነው የሚረጨው። ውስኪ ይጨለጣል። ቮድካ ይለጋል። የሚያጣጡም አሉ። የጓሮ መውጫ ስላለ “የደንቡን እያደረሱ ቢሆንስ” ቁርጥ፣ ውስኪ በገፍ ከገባ መቀንዘር አይቀርም። ለዚህም ነው አጣጮች የሚመጡት … ያበደው “ይህኔ ይብቃ” አለ። ቀበቶና ጮማ እኩል …

አዘግተው ሺሻ የሚምጉና ጫት የሚበሉ አሟሟቂ አላቸው። ጸሃይ የማይመታቸው ፍልቅቅ ህጻናት አባቶቻቸው ጎን ቁጭ ብለው በዝግ ቤት ሺሻ ይምጋሉ። ሲግልና ሲጋጋሉ አባቶቻቸው ስር ይገባሉ። አንዳንዶቹ ልክ ህጻን አብልተውና አጠጥተው የሚያስገሱ ይመስል ጩጪዎቹን ደረታቸው ስር ለጥፈው ይምጉዋቸዋል። አሻሻጮቹ ኮማሪዎች/ ባለቤቶቹ ማለት ነው ለቅኝት ብቅ እያሉ ዳሌ አስገምግመው፣ በምልክት ማነቃቂያ አሳይተው ይሸበለላሉ። ዝግ ቤቶች …

ያበደው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት በዝርዝር ሪፖርት ለማቅረብ ቀጠሮ መያዝ አስቧል። ሳይያዝለትም አይቀርም። ቦሰና መስመሩን አበጅታለታለች። “የሚሰማ ካለ ይስማ” ብሎ ፋይል እያደራጀ ነው። አሁን አሁን ሌብነቱ፣ መርከስከሱ፣ በዝግ ቤት፣ በቪአይፒ ቁርጥ ቤት፣ በድለላ፣ በክህደት፣ በነጻ አውጪዎች ጋጋታ፣ የፖለቲካ ነጋዴዎችና ቅምጥ ሚዲያዎች በድምሩ ህዝቡ ላይ ተባብረው የነገሱ ይመስላሉ። ሁሉም ነገር ገሃድ የተፈቀደ እስኪመስል በአደባባይ ሆኗል። መልክሞች አልፎ አልፎ ቢኖሩም እነዚህኞቹ በዘመቻ ሳያሰለሱ ቀን በቀን ተናበው ይዘምቱባቸዋል። ቤተስብ፣ ዘመድ፣ ልጆችና ወዳጆቻቸው ሳይቀሩ እረፍት እንዲያጡ ይሆናሉ። ተናቦ ኢትዮጵያን ማንደድ የዚህ ፓኬጅ አካል ነው!!

ቁርጥ ቤት በአሜሪካ – ያበደው የማይረሳ ታሪክ ገጥሞታል። የዩቲዩብ አክተሮች ስጋ ተሰብስበው እየበሉ አያቸው። ሁለት እመቤቶች አብረው ስጋ ሊበሉ ገቡና ያበደው አቅራዲያ ታደሙ። አዘዙና ዙሪያቸውን ሲቃኙ በላይ በላይ እያስጨመሩ የሚቆርጡትን የዩቲዩብ አክተሮች አዩ ። ሲሳይ አጌና አልነበረም። እነደተማከረ አበዱ። ዘለሉ። ” አፈር ብሉ፤ እመቤቴ ደም ታድርግባችሁ፤ ህዝብ እያጫረሳችሁ እናንተ እዚህ ስጋ ትበላላችሁ…” እሳተ ጎሞራ ተፉባቸው። ” የወላድ እምባ ይፍረድብቸሁ ” ተራገሙ።

ከውጭ ሆኖ የሚነቀንቀውም ነጋዴ ነው። ከውስጥ ሆኖ የሚነቀነቀውም ነጋዴ ነው። ነጻ አውጪው ቆራጭ ነው። እዛም ቆራጭ እዚህም ቆራጭ ነው። የከርስ ፖለቲካ አይሞላም። የከስርስ ፖለቲካ ከርሳቸው የጎደለ ሁሉ እንዲሸጡ ያደርጋቸዋል። የከርስ ፖለቲካ ድንኳኑንን የትም ይጥላል። ከኦነግ ሸኔም ከኤርትራም ይለምናል። ከሻዕቢያ ቂጥ ስር ያልከሰክሳል፤ ሲያድግ ከግብጽም ይወስዳል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከርስ ላይ ስለተተከለ አዘኔታ የለውም። ያለፉት ሰላሳ ዓመታት ጨዋታ በከርስ መግዛት ስለነበር ገና ይቀጥላል። ከርስ ” የማበስበሻ” ስልት ነው። ትህነግ በከርስ አብስብሶ ነበር የሚነዳቸው። ከርስ ሲበለጽግ ቪአይፒ ስጋ ቤት እንጂ አርሶ አደር ማሳ ሂዲ ሂዱ አይልም። የከርስ ፖለቲካ …

ያበደው ብዙ ሰምቷል። ለዛሬ ወራጅ አለ ይላል። ቦሰናም ጊዜ ትፈልጋለች። ቦሰና በጊዜው ቀልድ አታውቅም። አትደራደርም። ጥሬ ስጋ ነብሷ ነው። ስጋ ታውቃለች። ማንም ቀበቶ አይሰጣትም። “አኞህን ተውና ለካድሬዎቹ ከምትደብቀው ቁረጥ” እያለች ታሳየዋለች። ቦሰና ጥሬ ከቀመሰች ደረቅ ጠጅ እንጂ ሌላ ማግበስበስ አትወድም። ከዛ በሁዋላ ” በሉ እንጂ” ታዘፍናለች። እናንተም ዝፈኑ… ሰላም ሁኑ!! እናንተ ከሰውነት ይወረዳችሁ ሟቾች “ሰው ሁኑ። አትኮፈሱ። ከዚአይፒ ውጡና የቀበሌ ነዋሪ ሁኑ” ይህ የደጎል የውሻው ምክር ነው!!

See also  [መቅመል፣ ቅማላም] - በሁለት ረድፍ

Leave a Reply