የነርቭ ዘንግ ከህብረሰረሰርና ከአንጎል ተነስተው በአስቸጋሪ ና ጠመዝማዛ መንገድ ወደ ምድብ ቦታቸው ይጓዛሉ።ልክ ጥሻና ጎርባጣ መንገድ የመጓዝ ያክል መንገዳቸው ጥልፍልፍና ውስብስብ ነው የነርቭ ዘንጎች ጉዞ።
አብዛኛውን ግዜ ከወጣትነት የእድሜ ክልል አንስቶ እስክ ጣሪያው ያሉ የሰዉ ልጆችን በሙሉ ሊያጠቃ የሚችል ህመም የሚሰራጭ የወገብ ነርቭ ህመም በተለምዶ sciatica ተብሎ ይጠራል።ይኸም ለወገብና ለእግር የሚያስፈልጉ የነርቭ ዘንጎች በጥቃት ሲጎዱ የሚፈጠር የትኛውንም ምልክት የሚወክል ነው።
ስያሜው ፍትሐዊ እና ሁሉን ያቀፈ ስላልሆነ የተዛባ ስያሜ/ Misnomer / ብለው ይጠሩታል የህክምና ጠበብቶቹ፤ማለትም ሺያቲካ ከሚባል ትልቅ የነርቭ ዘንግ የመነጨ ቢሆንም ግን ሌሎች የነርቭ ዘንጎች ሲጠቁም ስያሜው ተመሳሳይ ነው።ለዚያ ነው የተዛባ ስያሜ ሊባል ያስቻለው።
sciatica በህክምና ባለሙያዎች እንደ አንድ የህመም ምድብ ተደርጎ አይታይም፤በሰፊው ማህበረሰብ ዘንድ ግን የተለመደና በሰፊው ጥቅም ላይ የዋለ መጠሪያ ነው።
ወገብ ህመምና የሚሰራጭ የወገብ ነርቭ ህመም የተለያዩ ናቸው።ወገብ ህመም ሁሉ የነርቭ ችግር አይደለም፤የነርቭ ችግር ሁሉም የወገብ ህመም ሊያመጣ አይችልም።
የሚሰራጭ የወገብ የነርብ ዘንግ ህመም ሲባል ህመሙ በአንደኛው ወገብ ጀምሮ ወደ ታች ደረጃ በደረጃ የሚሰማ ህመም ነው።ከ ወገብ->ዳሌ->ጭን->እግር->ውስጥ እግር ድረስ በተለያየ መጠንና አቅጣጫ የሚሰማ የማቃጠል፣መለብለብ፣መጋል መንደድ፣መደንዘዝ፣መስነፍ ፣..ምልክቶች የሺያቲካ ምልክቶች ናቸው።ምልክቶቹ አንዳንዶቹ ሲቀመጡ፣ሲጓዙ፣በጀርባ ሲተኙ ፣በጎን ሲተኙ ህመማቸው ሊባባስ ይችላል፤ለሌሎቹ በነዚህ አጋጣሚዎች ሊሻሻል ይችል ይሆናል።
ታማሚዎች ህመሙን በተለያየ አገላለፅ ሲገልጡት ይታያሉ።አንዳንዶቹ እንደ ፍም እሳት የሚያነድ፤ ሌሎች እንደ ኤሌክትሪክ የሚነዝር ሲሉት ቀሪዎቹ እንደ ጋለ ብረት ምጣድ የሚያንሰፈስፍ ብለው ይጠሩታል።ከህመሙ በተጨማሪ እንደ በረዶ መቀዝቀዝ አልፎ አልፎም የጡንቻ መዛል ተያያዥ የችግሩ ምልክቶች ሆነው ይታያሉ።
ለዚህ እንደ አጋላጭና ምክነያት:-….
1) እግርን ለብዙ ግዜ አጣምሮ መቆየት፦እግርን አጣምሮ መቀመጥ በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ነው።እንደዚህ አይነት ልማድ ዉደ እግር ለሚጓዙ የነርቭ ዘንጎች ምቾት የሚሰጥ አይደለም።
እግር ሲጣመር በታችኛው ወገብና በዳሌ ላይ ባሉ የጡንቻና አጥንት አቀማመጥ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ያደርጋል።ይኸ ሲሆን ተሹለክልከውና ተጠማዘው በሚጓዙ ነርቭ ዘንጎች ላይ አካላዊ ጫና ያሳድራል።ይኸኔ ነው ነርቮቹ መጎዳታቸውን ለማሳወቅ አመላካች ምልክቶች ያሳያሉ።ምልክቶቹ የድረሱልኝ ጥሪዎች ናቸው።
እግርዎን ከቻሉ አያጣምሩ ካልቻሉ ቶሎ ቶሎ ይቀያይሩ፤
2) በሗላ ኪስ ቦርሳ/ዋሌት/ አድርጎ መቀመጥ:- ይኸ የወንዶች ጉዳይ ነው።ሴቶች ….ጉዳዩን በግልባጭ ካልሆነ የችግሩ ተጠቂዎች አይደሉም ብዬ አስባለሁ።
አዎ! የኪስ ቦርሳ በተለይ በወረቀቶች የተወጠረ ኪስ አድርጎ መቀመጥ በዳሌ ጡንቻ ላይ ችግር ይፈጥራል።ጡንቻዎቹ ሲጎዱ ሸፍናውና አሽሞንሙነው በሚያሳልፏቸው የነርቭ ዘንጎች ላይ ጉዳት ይፈጥራል።
3) የተዛባ አቀማመጥ:-በማወቅም ባለማወቅ ሰዎች ሲቀመጡ ወገባቸውን ፣መቀሙጫቸውን ወደ አንድ አቅጣጫ (ወደ ጎን፣ወደ ፊት፣ወደ ሗላ…) አዛንፈው ነው።የሰውነት ክብደት ምጥጥንን ያልጠበቀና ተፈጥሯዊ የነርቭ መሿለኪያ መስመሮችን የሚያጠብ በመሆኑ ለከፋ የነርቭ ችግር አጋላጭ ነው።ሲቀመጡ ወደ አንድ ሳያዳሉ ለግራና ቀኝ ክፍሎች እኩል በሆነ መጠን መቀመጥ ተገቢ ነው።
አንዳንድ ታክሲ ላይ ጋቤና ያለቺው ሁለተኛዋ ወንበር ለብዙ ሰዎች ምቾት የምትሰጥ አይደለችም።ሌላው ደረቅ ነገር ላይ አብዝቶ መቀመጥ ለጉዳት ያጋልጋል።
4)የጀርባ ሸክም የሚሸከሙ:- የዱሮ እናቶች እንስራ በጀርባቸው ይሸከሙ ነበር፤ዛሬ ከሞላ ጎደል ቢቀርም አሁንም በልዩ ምክነያቶች በጀርባ የመሸከም ልማድ ይታያል።ተጨማሪ መንስኤዎች።
የአጥንት መሳሳት፣የፀሐይ እጥረት፣የአጥንት ማደግ፣የነርቭ መውጫ መሿለኪያዎች መጥበብ ፣የመገጣጠሚያ ብግነትና መጋጨት፣የዲስክ መሸራተት ፣…ዋና መንስኤዎች ናቸው።በኛ ሀገር የነርቭ መሿለኪያ መጥበብ(spinal canal and inter/intra foramina stenosis) በጣም በዝቶ እናገኘዋለን።የቫይታሚን ዲ እጥረት ተጠቃሽ ነው።
እንደዚህ አይነት ህመም በእርጉዝ እናት ላይ ሊከሰት ይችላል።
ይኸም የሚሆነው በማህፀን መስፋፋትና ማደግ በሚከሰት አካላዊ ጫና አማካኝነት ነው።ከወሊድ በሗላ ጫናው ሲጠፋ የሚስተካከል ነው።ችግሩን አጣዳፊና ለዘብተኛ ብለን እንከፍለዋለን።አጣዳፊ ሲባል በቶል የቀድ ህክምና አገልግሎት የሚፈልገውን ነው።ድንገተኛ ህመም ከሚከተሉት ተጓዳኝ ምልክቶች ጋር ተጣምሮ ሲከሰት አጣዳፊ ምድብን ይወክላል:-
ሀ) የሽንት/ሰገራ ማስወገድ ችግር፤ለ) ሁለቱንም እግሮች ሲያካልል፤ሐ) የእግር መስነፍ፤መ) ህመሙ አሰቃቂና ፋታ የማይሰጥ ሆኖ ይከሰታል።
እነዚህ ምልክቶች ካሉ አስቸኳይ የወገብና ህብረሰረሰር ምስለ ምርመርራ ያስፈልጋል፤በውጤቱ መሰረት ተገቢውን ህክምና በአፋጣኝ መስጠት ይገባል።ከቀዶ ህክምና እስከ ክኒን ህክምና አማራጭ አለው። የሰውነት እይቅስቃሴ እና ማጎልመሻ እንዲያደርጉ ይመከራል።
ዘልማዶችን ማስቀረት፣ሸክም ማስቀረት፣ፀሐይ መሞቅ፣ክብደትን ማስተካከል፤አመጋገብን ጤናማ ማድረግ፣ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣አካላዊ እይቅስቃሴ ማድረግ መከላከያና ማከሚያ ስልቶች ናቸው።
ተገቢውን የሐኪም ምክር ያግኙ፤ይታከሙ፤እራስዎንም ያክሙ!
ዶር መስፍን በኃይሉ፤ጥቁር አንበሳ
በቴሌግራም ያግኙን t.me/HakimEthio