አዋጭነታቸው ያልተረጋገጠ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በጀት እንደማይመደብላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

NEWS

ከቀጣዩ በጀት ዓመት ጀምሮ አዋጭነታቸው ያልተረጋገጠ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በጀት እንደማይመደብላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ የግዥ ሥርዓቱን ማዘመን ዓላማ ያደረገ የግዥ ማሻሻያ አዋጅ መዘጋጀቱንም ገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። አዋጭነታቸው ሳይረጋገጥ በጀት የሚመደብላቸው የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ለሃብት ብክነትና ለግንባታ መጓተት መንስዔ መሆናቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

መንግሥት ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የፌዴራል መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር አዋጅ ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።

በአዋጁ መሰረት በፕላንና ልማት ኮሚሽን ታይቶና ተገምግሞ አዋጭነቱ ያልተረጋገጠ ፕሮጀክት በጀት እንደማይመደብለት በግልጽ ማስቀመጡን ጠቅሰዋል።

በዚሁ መሰረት መንግሥት ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ አዋጭነታቸው ላልተረጋገጠ የልማት ፕሮጀክቶች በጀት መመደብ እንደሚያቆም ነው ያስታወቁት።

የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ መሰረት የተቀመጠላቸውና በግንባታ ላይ የሚገኙ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ይህ ተግባራዊ መደረጉ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁና የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ከማድረግ አኳያ ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት።

የገንዘብ ሚኒስቴር በአጠቃላይ ፕሮጀክቶችን መቆጣጠር የሚያስችለውን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱንና የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግምገማን መሰረት በማድረግ ገንዘብ እንደሚለቀቅም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የተንዛዛውን የግዥ ሥርዓት እንደሚቀይርና እንደሚያዘምን የታመነበት የግዥ ማሻሻያ አዋጅ መዘጋጀቱን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት።

እንደ ዶክተር እዮብ ገለጻ በኢትዮጵያ ያለው ረጅምና የተንዛዛ የግዥ ሥርዓት ሀገሪቷን ተጠቃሚ ያላደረገና ውጤታማም እንዳልሆነ በመንግሥት ተገምግሟል።

ለዚህም የግዥ ሥርዓቱን በማዘመን አሁን ያለውን ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀይር የታመነበት የግዥ ማሻሻያ አዋጅ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

አዋጁ ግዥዎችን በአጭር ጊዜ መከወን የሚያስችልና ትልቅ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች በግዥ ጨረታ ሂደት እንዲሳተፉ ማድረግ የሚያስችሉ ሕጋዊ ማዕቀፎችን መያዙን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው የግዥ ሂደት አነስተኛ አቅም ያላቸው ተቋማት እንዲሳተፉ የሚያደርግ እንደሆነና በተሻሻለው አዋጅ ተጫራቾች የጨረታ ማስያዣ ቦንድ /ቢድ ቦንድ/ እንዲያስይዙ እንደሚያስገድድ ጠቁመዋል። ይህ መሆኑ ትልቅ አቅም ያላቸው ድርጅቶች በጨረታዎች ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የጠቆሙት።

የግዥ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እየታየ እንደሚገኝና በተያዘው በጀት ዓመት ፀድቆ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

የውጭ ኩባንያዎች ብቻ እቃ በዱቤ ከውጭ ሀገር እንዲያስገቡ የሚያደርገውን መመሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያሻሻለው እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እየተሻሻለ ያለው መመሪያ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እቃ በዱቤ ከውጭ ሀገር እንዲያስገቡ እንደሚፈቅድ ይሄም ባለሀብቶችን ለማበረታታት አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው በቅርቡ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምርም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ ማሻሻያዎች የተደረጉበት የታሪፍ መጽሐፍም ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚካሄድበት ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው የታሪፍ መጽሐፍ አምራቹን የማይደግፍ፣ የገቢ ንግድን የሚያበረታታና የቀረጥ ምጣኔውን ምርትና ምርታማነት የማያበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መጽሐፉ የነበሩ የአሠራር ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ያስቀመጠና አምራቾችን የሚያተጉ ማበረታቻዎችን እንደያዘም ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የታክስና የቀረጥ እፎይታዎችን በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ብቻ እንዲሰጡ የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

(አብመድ)

Related posts:

"መከላከያ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል በሚችልበት አስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል" አብይ አህመድ
መንግስት "በመላው አገሪቱ ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰድኩ ነው"- የትህነግ ሰርጎ ገቦች ላይም እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ
አቶ ወርቁ አይተነው የገንዘብ ቀውስ እየገጠማቸው መሆኑ ተሰማ
ብ/ጄ ተፈራ ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ
አውሮፓ ህብረት ያዘገየውን ድጋፍ አስመልክቶ ዳግም ሊመክር ቀጠሮ ያዘ
«ሕወሓት ጦርነትን እንደ አምልኮ የሚቆጥር ቡድን ነው» – ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ
«በሕገወጦች ላይ ያለ ምኅረት እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይህ የመንግሥት ተግባር ነው» የአማራ ክልል
125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ
«በአገሩ መከላከያ ላይ አፉን የሚከፍት ሕዝብ የለም፤ መንግስትም አይታገስም» ክብር ለመከላከያ ሰራዊት!!
በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል የተደረገውን የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት ምክር ቤቱ አጸደቀ
የሞት ፍርደኛው የ25 ዓመታት ሰቆቃ! ከመሬት በታች የታፈኑት አባት
«ኢትዮዽያን ማስቀጠል ከሚፈልጉት ጎን በመሆናችን የሚከፋ ከአለ እርሱ መፍረሷን የሚናፍቅ ብቻ ነው!»
ደብዳቤ ለኢትዮጵያ - ከቢልለኔ ስዩም
የዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ፈረመ
"እናቴ ፍጹም እስር ቤት እንድትገባ አልፈግም" ብሎ እግሩን ያጣው ወጣት ምስክርነት ለሮይተርስ

Leave a Reply