ጣልያን ከዓድዋ ሽንፈት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን ስትወር ለረጅም ጊዜ የመግዛት ህልም እንደነበራት ፣ይህንንም እውን ለማድረግ ህዝቡን በጎሳና በብሄር የመከፋፈል ስልት ትጠቀም እንደነበር የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ልጅ ታቦር ገረሱ ገለጹ። የፋሺስት ጣልያን ጦር ከኢትዮጵያ ተባሮ ከወጣ በኋላም እንግሊዞች ኢትዮጵያን ለመከፋፈል በዚሁ መልኩ ሙከራ አድርገው እንደነበር ጠቆሙ።

አቶ ታቦር ገረሱ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ወቅት ጣልያኖች ኢትዮጵያን አስከመጨረሻ በቅኝ ግዛት ስር ለማድረግ ብዙ ሙከራ ቢያደርጉም ህዝቡ ግን አልተቀበላቸውም ነበር። በተለይ ወረራውን ባለመቀበል በየዱር ገደሉ ሸፍተው የነበሩ አርበኞች በወራሪው ኃይል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ፤አባታቸውም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ወራሪዎችን መቆሚያ መቀመጫ ካሳጡ ጀግኖች አንዱ ነበሩ።

ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ከልጅነታቸው ጀምሮ ከአልጋወራሽ አስፋወሰን ጋር የኖሩ በመሆናቸው ለእሳቸውም ሆነ ለሃገራቸው ትልቅ ፍቅርና አክብሮት እንደነበራቸው የጠቆሙት አቶ ታቦር ፣ ጣልያን ኢትዮጵያን ሲወር ወደውጭ ከመውጣት ይልቅ እዚሁ በመቅረት የተለያዩ ሃገር ወዳድ አርበኞችን በማሰባሰብ ጣልያንን ሲዋጉ ቆይተዋል ብለዋል።

በአባታቸው የሚመራው አርበኞች ጦር በተለይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ እስከ ወላይታ ድረስ በተለያዩ ስፍራዎች ከጣልያን ጋር በግንባር በመግጠም ጭምር ከፍተኛ የጦር መሳርያ እስከመማረክ የደረሰ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ታቦር ፣ጣልያንም በእነዚህ አርበኞች የሚደርስበትን ጥቃት ለመከላከል በአውሮፕላን ጭምር እስከመደብደብ ደርሶ እንደነበር ጠቁመዋል።

አቶ ታቦር እንደገለጹት ደጃዝማች ገረሱ ከ15 ሺህ በላይ የጦር ሠራዊት የነበራቸው ሲሆን፤ በዚህም ጣልያን በተለያዩ ወቅቶች አንዴ በኃይል ሌላ ጊዜ ደግሞ በድርድር እሳቸውን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ሙከራ ማድረጋቸውን አመልክተዋል። ደጃዝማች ገረሱ ፈቃደኛ ሆነው ለጣልያን ከተገዙ ከፍተኛ ሹመት እንደሚሰጧቸው ጭምር መልዕክተኛ በመላክ ሙከራ ማድረጋቸውን፤ አባታቸው ለዚህ ፈቃደኛ እንዳልነበሩ አስታውቀዋል።

(ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply