” ከአዲሱ የኢትዮጵያ ካርታ ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጨዉ መረጃ ተቀባይነት የሌለዉና መወገዝ ያለበት ነዉ”

” ከአዲሱ የኢትዮጵያ ካርታ ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጨዉ መረጃ ተቀባይነት የሌለዉና መወገዝ ያለበት ነዉ።”-የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በሃገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ስራና በአጠቃላይ የኮሚሽኑ ሁኔታ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዶ/ር ጣሰዉ ገብሬ ኮሚሽኑ እስካሁን ደረስ ሲሰራ የነበረዉን አጠቃላይ የጥናትና ምርምር ስራ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ከአስተዳደራዊ ወሰኖች: ከማንነትና ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማድረግ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦችን ለማዘጋጀትና ለማቅረብ የተቋቋመ ኮሚሽን ነዉ።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ እንደተናገሩት ከሰኔ 2012 ጀምሮ በአስተዳደር ወሰን: የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ስራ ሲያከናዉን እንደነበር ተናግረዋል።

ጥናትና ምርምሩ በፊንፊኔ ዩኒቨርስቲ ባለቤትነት የሚመራ መሆኑን የተናገሩት ሰብሳቢዉ ሌሎች ችግሮች ባሉባቸዉ አካባቢዎች 28 ዩኒቨርስቲዎች የተሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በጥናቱ 56 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተሸፈኑና 70 ተመራማሪዎችና በርካታ መረጃ ሰብሳቢዎች የተሳተፉበት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ጣሰዉ ገብሬ በተለያዩ ሁኔታዎች ማለትም በድርሳናት ዳሰሳ/ክለሳ: በቁልፍ መረጃ ሰጪ ቃለ ምልልስ: የትኩረት ቡድን ዉይይት እና ቤት ለቤት በታብሌት የታገዘ የቤተሰብ መረጃ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

በማንነት: ራስን በራስ በማስተዳደር: በአስተዳደር ወሰን እና የሕግና ፖሊሲ አማራጮች ዙሪያ አራት የተጠቃለለ የጥናትና ምርምር ሪፖርት መቅረቡንም ገልጸዋል።

በተደረገዉ ጥናትና ምርምር ዉስጥ ከመዋቅራዊ አደረጃጀት ጋር የተገናኘ ግኝት የሚተካተተበት መሆኑን እና በቀረበዉ ሃገራዊ የጥናት ዉጤት ላይ ተከታታይ የባለድርሻ አካላት ዉይይትና ግብአት በማካተትና በማዳበር ይፋ እንደሚደረግም በመግለጫቸዉ ጠቅሰዋል።

ጥናትና ምርምሩ ለ18 ወራት ሲካሄድ የነበረ ሲሆን ጥናትና ምርምር ለማካሄድ ከተመረጡ 68 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች መካከል በ12 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በጸጥታ ችግሮችና በተያያዥ ምክንያቶች ጥናትና ምርምሩ አልተካተተም።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸዉ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አዲሱ የኢትዮጵያ ካርታ ነዉ በማለት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቀዉ መረጃ መሠረተ ቢስና መወገዝ ያለበት ነዉ ብለዋል።

ወንድማገኝ አሰፋ

Leave a Reply