dr bethelem

በሶማሌ ክልል በዘጠኙም ዞኖች ዝናብ ጠብ አላለም። ከብት እምሽክ ብሏል። የክልሉ መሪ እንዳሉት ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንሳሳት ድርቅ በልቷቸዋል። በውሃ ጥምና ችጋር በሺህ የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል። አስቸኳይ ርብርብ ካልተደረገና ዝናቡ ወደፊትም ካልዘነበ ክልሉ ውስጥ ያሉ ከብቶች እንደሚያልቁ፣ ሕዝቡም እጣ ፈንታው ሞት ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው። ለሶማሌ ሕዝብ ማን ይጩህ?

ድርቁ ያስከተለውን ችግርና የችግሩን መጠን በቅርብ የሚከታተሉ እንደሚሉት አሁን ከሆነው በላይ መጪው ጊዜ ከባድ ነው። ድርቁ አስከትሎት የሚያልፈውን ችግር ለመቋቋምም ቀላል አይሆንም። በየአቅጣጫው ያሉ ተፈናቃዮች፣ የድርቅ ተጠቂዎች፣ የትህነግ አመራሮች መንግስት እህል፣ መድሃኒት፣ ልብስ፣ ንጹህ ውሃ እንዲያቀርብ እየወተወቱና እየወቀሱ ነው። መንግስት ከውጭ አገር እርዳታና ብድር እንዳያገኝ በቀኝ እጃቸው እየሰሩ፣ ዳግም መልሰው መንግስት ላይ ተቃውሞ የሚሰነዝሩ ተከፋይ ሚዲያዎችና ሽፍቶች፣ የፖለቲካ ድርጅት ሃላፊዎችና ሁለት ቦታ የሚጫወቱ አንድ ላይ ሆነው የሕዝቡን መከራ እያራዘሙት እንደሆነ ከየአቅጣጫው ቅሬታ እየቀረበ ነው።

ውሃ በቦቴ እየተመላለሰና መኖ እየተጓጓዘ ለማትረፍ የሚደረገው ጥረት ይህን ይመስላል

በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምልከታ ካደረገ በሁዋላ አስታውቋል። ቋሚ ኮሚቴው በሸበሌ ዞን ሁለት የመጠለያ ጣቢያዎች በድርቁ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ካየ በሁዋላ ምክትል ሰብሳቢዋ ዶ/ር ቤተልሔም ላቀው አማካይነት የችግሩን አሳሳቢነት የገለጸበት መነግደ ያሳዝናል።

የክልሉ አመራር ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት ለመከላከል በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ቤተልሄም፣ የድርቁን አሳሳቢነትና እያስከተለ ያለውን ጉዳት የሚዲያ ሽፋን በመስጠት የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ አውቆት ተገቢውን እርዳታ እንዲሰጥ ከማድረግ አንፃር የክልሉ መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ቃል በቃል አይግለጹት እንጂ መልዕክታቸው መጠነኛም ቢሆን መፋዘዝ እንዳለ አመላካች ሆኗል።

በሸበሌ ዞን በሁለቱም የመጠለያ ጣቢያዎች ሶስት ሺህ 960 አባወራዎች በድርቅ የተፈናቀሉ ሲሆኑ እየተደረገ ያለው ድጋፍ የምግብ፣ ውሃ እና የህክምና አገልግሎት በመንግስት እና በረድኤት ድርጅቶች አማካኝነት ቢሆንም አቅርቦቱ ተመጣጣኝ አለመሆኑን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል፡፡ ችግሩን በተባበረ ክንድ ለመቀልበስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመተጋገዝ የዜጎችን ህይወት መታደግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በአንድ ቦታ ብቻ የታየው ይህ ችግር በድፍን ሶማሌ ክልል ምን እየሆነ እንደሆነ ያሳያል። የክልሉ ሕዝብ በዚህ የመኖርና ያለመኖር መከራ ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በሶማሌ ክልል ላይ ጦር ለመስበቅ ሽፍቶችን ከሚያደራጀው ትህነግ ጋር በኬንያ እየመከሩ ያሉ የሶማሌ ክልል ተወላጆች ለድርቁ እስካሁን አንዳችም እርዳታም ሆነ ድጋፍ አለማድረጋቸው በአሳፋሪ ታሪክነት እንደሚቀመጥ ነዋሪነታቸውን ሲውዲን ያደረጉ ለኢትዮ12 ተናግረዋል። የሶማሌ ክልል ለምሳሌ ተነሳ እንጂ በአምራም ሆነ በኦሮሚያ ተመሳሳይ ችግር አለ። በትግራይም እንደዚሁ።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ የቋሚ ኮሚቴው አባላት የህዝብ ውክልናን በአግባቡ ለመወጣት ላደረጉት የመስክ ምልከታ አመስግነው፤ የድርቁ አስከፊነት ለአርባ ዓመት ታይቶ የማይታወቅ በመሆኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአርብቶ አደሩ እንስሳት መሞታቸውን መናገራቸውንና በዘጠኝ ዞኖች ምንም ዝናብ ባለመዝነቡ የተከሰተው ድርቅ የተለየ በመሆኑ የክልሉ መንግስት በማስገባት 15 ሚሊዮን ብር በመመደብ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የውሃ፣ ምግብና የመድሃኒት አቅርቦት መደረጉን ጠቁመው በቀጣይም ዝናብ ካልዘነበ የድርቁ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ የፌዴራል መንግስት ተጨማሪ በጀት መፍቀድ እንዳለበት መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ጠቅሶ ኢዜአ ከዘገበው ላይ ቀንጭበን አስፍረናል።

Leave a Reply