150 ሺህ የቀበሌ ቤቶችን ኦዲት ሊደረጉ ነው

በአዲስ አበባ የሚገኙ 150 ሺህ የቀበሌ ቤቶችን ኦዲት ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የሱፍ ኢብራሂም ትናንት የተቋሙን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ባለስልጣኑ በከተማዋ የሚገኙ 150 ሺህ የቀበሌ ቤቶች ላይ የኦዲት ሥራ ያከናውናል።

የኦዲቱ ሥራው የቀበሌ ንግድ ቤቶችንና መኖሪያ ቤቶችን የሚያካትት ሲሆን፤ የማጣራት ሥራው የሚከናወነው በየክፍለ ከተሞች ካሉ አመራሮች ጋር ነው ብለዋል።

የቀበሌ ቤቶች ጉዳይ ሰፊ የፍትህ ጥያቄና ቅሬታ የሚቀርብበት ነው ያሉት አቶ የሱፍ፤ ሥራው ሲጠናቀቅ ግልጽነት ያለው አሠራር ለመዘርጋት ይረዳል። በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩም ምን ያህል ቤት በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳለው በቂ መረጃ ለመያዝ እንደሚረዳው አስታውቀዋል።

በዚህ ረገድ የኦዲት ምርመራው ከኅብረተሰቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎችንም መረጃን መሠረት በማድረግ ለመፍታት እንደሚጠቅም ተናግረዋል።

 ዛሬም ድረስ በከተማዋ ንብረቶችን በማዘዋወርና በመጠቀም ረገድ ክፍተት እንዳለ ጠቁመው፤ ይህም ለብክነትና ለሌብነት በር እየከፈተ ከፍተኛ የመንግሥት ሀብት እየጠፋ እየተሰረቀና እየወደመ ይገኛል ብለዋል።

ምርመራው የመንግሥት ንብረትን በማስተዳደር ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል እንደሚረዳ ገልጸዋል።

በባለስልጣኑ የዕቅድና በጀት ክፍል ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ አለሙ በበኩላቸው ተቋሙ በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ንብረቶችንና ሕንፃዎችን የመቆጣጠርና የማስተዳደር ኃላፊነት አንደተሰጠው በመጠቆም፤ በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉትን ንብረቶች ላይ በሙሉ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል።

እስካሁን በከተማዋ 4 ሺህ 80 ሕንፃዎች መመዝገባቸውንና 689 ንብረት ያላቸው ተቋማት መኖራቸውን ጠቁመዋል። እነዚህ ተቋማት በሙሉ ንብረታቸው እንዲቆጠር ይደረጋል። ንብረቶቹም ተመዝግበው የትኛው ንብረት አስፈላጊው ጥቅም ውሏል? የትኞቹን በተገቢው ጥቅም ላይ አልዋሉም? የሚለውን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ይቀመጣል ብለዋል።

በዚህ ረገድ እስካሁን በተከናወኑ የቁጥጥር ሥራዎች በኮልፌ ክፍለ ከተማ ዘጠኝ ባለቤት አልባ ሕንፃዎች መገኘታቸውን የጠቆሙት አቶ ቴዎድሮስ፤ እነዚህንም በፍርድ ቤት አሳውጆ ተረክቦ ለማስተዳደር ሂደት መጀመሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ወጥ የሆነ የቢሮና የቁሳቁስ ስታንዳርድ እንዲኖራቸው የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።

ለዚህ እየተዘጋጀ ያለው ስታንዳርድ ሲጠናቀቅ እያንዳንዱ አመራርም ሆነ ባለሙያ የሚጠቀምባቸው ዕቃዎች ግዢ የሚፈጸመው በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ይሆናል። ይህም አላግባብ ለግዢ የሚወጡ የተጋነኑ ወጪዎችን ለመቀነስ እንደሚረዳ አስታውቀዋል።

 ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 7 /2014

Leave a Reply