• ፖሊስ ተከሳሹን ፈልጎ እንዳጣ ቢናገርም ተከሳሹ ግን በድብቅ ችሎት እየገባ ክሱን አዳምጦ ይወጣ ነበር።

አቢሲኒያ ባንክን የ6.1ሚሊዮን ብር አሳጥተዋል ተብለው በከባድ ሙስና ወንጀል ከተከሰሱ ከ 5 ተከሳሾች መካከል አንደኛ ተከሳሽ አይተንፍሱ እንዳሻው ይባላል።

ይህ ተከሳሽ ክስ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርበው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር።

በመጨረሻም ፖሊስ ተከሳሹን በመኖሪያ አድራሻው አፈላልጎ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጾ መልስ መስጠቱን ተከትሎ ተከሳሹ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግለት ተደርጓል። ከጋዜጣ ጥሪው በኋላ ተከሳሹ በችሎት አለመቅረቡን ተከትሎ በሌለበት መዝገቡ እንዲቀጥል ብይን ተሰጥቶ ነበር።

ይሁንና ግን ተከሳሹ ክስ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ የችሎቱ ዳኞች በአካል ስለማይለዩት ተደብቆ ችሎት እየገባ ምን እንደተባለ አዳምጦ ሾልኮ ይወጣ ነበር። በዚህ መልኩ ተከሳሹ ተደብቆ ሲገባ አንደኛዋ ተከሳሽ ለፍርድ ቤት ለሚገኙ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር እንዲያውሉት ብትጠቁማቸውም በቁጥጥር ስር ሳያውሉት ቀርተዋል። ተከሳሹም ሳይያዝ ከችሎት ወጥቶ ይሄዳል። ይህንን ሁኔታ ተከሳሿ ለችሎቱ ዳኞች ጥቆማ ሰጥታለች።

የችሎቱ ዳኞች አርብ ዕለት በነበረ ቀጠሮ ጉዳዩን ለማጣራት የተከሳሹ የአክስት ልጅ የሆነ በዚሁ መዝገብ ለቀረበ ግለሰብ ተከሳሹን በሚመለከት ጥያቄ አቅርበዋል።

”በቁጥጥር ስር ያልዋለውን አይተንፍሱ የሚባለው ተከሳሽ እዚህ ሲመጣ አይተኸዋል ወይ?” ተብሎ የቀረበለት ግለሰብም በበኩሉ ”አዎ አይቼዋለሁ፣ እኔ እንደሚፈለግ አላቅም እንጂ ፍርድ ቤት እየመጣ ተከታትሎ ሲሄድ አይቻለው” ሲል መልስ ሰጥቷል።

ተከሳሹን ፖሊስ በአድራሻው ማግኘት አልቻልኩም ብሎ መልስ መስጠቱን ተከትሎ በሌለበት ጉዳዩ እንዲታይ ተብሎ ብይን ከተሰጠ በኋላ በዚህ ደረጃ ፍርድ ቤት ተደብቆ እየገባ ምን እንደተባለ አዳምጦ ሾልኮ ሲሄድ በቁጥጥር ስር የሚያውለው የፖሊስ አካል አለመኖሩ የችሎቱ ዳኞችን አበሳጭቷል።

ፖሊስ ለቆመለት አላማን መተግበር ሲገባው በቸልተኝነት ተከሳሹን ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ባለመዋሉ የተፈጠረ ችግር መሆኑን የችሎቱ ዳኞች ገልጸዋል።

”የዳኝነት ስራ ግልፅ ነው፣ የሚደበቅ ነገር የለም” ሲሉ ያብራሩት ሰብሳቢ ዳኛው የታሰረ ሰው ጥቆማ እየሰጠ ተከሳሹ ፍርድ ቤቱ ውስጥ ተደብቆ ገብቶ እየተንቀሳቀሰ ሌላው ማረሚያ ቤት ወርዶ የሚታይበት ሂደት በፍትህ ስርዓቱ ላይ መጥፎ አሻራ ጥሎ የሚያልፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ፍርድ ቤት ብቻ አደለም ያሉት ሰብሳቢ ዳኛው ፖሊስ ተከሳሾችን በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ እንደተቋም በተገቢ በጥረት ሊሰራ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።

እንደ አጠቃላይ ይህ መዝገብ በሚመለከት ችሎቱ ለታህሳስ 25 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶበታል።
ምንጭ: ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ

Leave a Reply