የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ቀላል እና ግልፅ ናቸው

የአማራ ህዝብ ሳይውል ሳያድር ሊፈቱለት የሚገባው ጥያቄዎች አሉት። እነዚህን ጥያቄዎች እንኳን አለመፍታት ማዘግየት በራሱ ይዞት የሚመጣው ዳፋ ከባድ እንደሚሆን ለመገመት ነብይ ጋር መዋልን አይጠይቅም። የአማራ ህዝብ ያለ ስሙ ስም ተሰጥቶት የጥላቻ ዶፍ እየወረደበት መኖር ከጀመረ ከ80 ዓመታት በላይ ተሻግሯል። በ1920’ዎቹ መጨረሻ አካባቢ የጀመረው ስም ማጠልሸት ዛሬ ላይ እጅና እግር አውጥቶ መራመድ ጀምሯል። ይኸ ህዝብ ያሳየው የበዛ ትግስት የሆነ ቦታ ላይ ማለቁ አይቀርም። ያኔ ነገሮች መበላሸታቸው እሙን ይሆናል። ይህ ከመሆኑ በፊት ፋታ ወስዶ ነገሮችን መመርመር ብልህነት ነው።

የአማራ ህዝብ ትልቅ ህዝብ ነው። ብዙ ቁጥር ከመያዙ ባለፈ ችግርን መቋቋም የሚችል፣ ገደልነው ሲሉት የሚነሳ፣ ሰፊ ትግስት የተላበሰ ህዝብ ነው። ለህዝቦች ነጻነት ልጆቹን ለዘመናት ገብሯል። የኋላ ታሪኩ የሚያሳየው ለነጻነት የተዋደቀ መሆኑን እንጅ ከሳሾቹ እንደሚሉት በዝባዥ፣ አቆርቋዥነት አይደለም። የዚህን ህዝብ ጥያቄ ችላ ብሎ ብዙ ርቀት መጓዝ የሚቻል አይሆንም። አሁን አሁን የሚታየው ግን ጥያቄዎቹን በአግባቡ በቅደም ተከተል ማዳመጥ እና ለመፍታት ከመነሳት ይልቅ ማጥላላት እና ተጨማሪ ስም ልጠፋ ሆኗል። ይኸ አካሄድ ሐገራችንን ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል እንዳይሆን ስጋት አለኝ።

የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ቀላል እና ግልፅ ናቸው። ስሜን አታጥፉ፣ አታፈናቅሉኝ፣ አትግደሉኝ፣ በእኩልነት እንኑር የሚሉ ናቸው። እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ቅን መሆን ብቻ በቂ ነው። የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች ለማዳመጥ እና ለመፍታት ከሚወጣው ጉልበት በላይ ጥያቄዎቹን ለመደፍጠጥ የሚወጣው ጉልበት የበዛ እየሆነ ነው። ቀላሉን መንገድ ትቶ አድካሚን መንገድ መከተል ምን ይፈይዳል ተብሎ እንደሆነ አላውቅም። በዚህ ከቀጠለ መጨረሻው ግን የማያምር እንደሚሆን ግልፅ ነው።

ለብሔር ብሔረሰብ ምሁራን የምናስተላልፈው አጭር መልዕክት ይኖረናል። የአማራ ህዝብ ከእኩልነት ያለፈ ጥያቄ የሌለው መሆኑን ማሳወቅ ነው። የአማራ ህዝብ ጥያቄ እንደ ሌሎች ጭቁን ህዝቦች ሁሉ ነጻነት እና እኩልነት ብቻ ነው። ይህንን በሚገባ እንደምትረዱት እናውቃለን። ስለሆነም ከአማራ ህዝብ ፍትሃዊ ጥያቄዎች ጎን እንድትቆሙ ጥሪ እናስተላልፋለን። ከአማራ ህዝብ ጥያቄ ጎን መቆም ከፍትህ ጎን መቆም፣ ከሰብዓዊነት ጎን መቆም መሆኑን በማወቅ ለህዝባችን ጥያቄ ጆሮ እንድትሰጡ አደራ እንላለን።

See also  ኧረ የሕግና የሕሊና ያለህ ?!

Gashaw meresha

Leave a Reply