ከሁለት ሺህ 700 በላይ አጠራጣሪ የፋይናንስ ማጭበርበር ጥቆማዎች ቀርቡ

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ሺህ 700 በላይ አጠራጣሪ የፋይናንስ ማጭበርበር ጥቆማዎች እንደደረሱትና አንድ መቶ ሰባ ሰባቱን ለሕግ አካላት ማስተላለፉን ገለጸ። ይህ የተገለጸው አገልግሎቱ ከፌዴራል የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር አዳማ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ እንደገለጹት አገልግሎቱ የሀገሪቷ የፋይናንስ ደህንነት ለማረጋገጥ ባንኮችና እንሹራንሶችን እንዲሁም ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

በተለይ በታክስ ማጭበርበር፣ ከህጋዊ የፋይናንስ ተቋማት ውጭ የሚንቀሳቀስ የውጭ ምንዛሪ ዙሪያ ከፍትህ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና ቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቀረቡት 2 ሺህ 700 አጠራጣሪ የፋይናንስ ጥቆማዎች ውስጥ 177 የሚሆኑትን አጠራጣሪ ጥቆማዎች በመለየትና በመተንተን ለህግ አካላት ማስተላለፉን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በህገ ወጥ መንገድ የተገኘውን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከ166 አገሮች ጋር መረጃ መለዋወጥ ተችሏል ብለዋል።

የተቋሙን አሰራር የማሻሻልና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ሪፎርም በመከናወን ላይ እንደሚገኝም አቶ ሙለቀን ተናግረዋል። መድረኩ ተግባር ተኮር የሆነ የፋይናንስ ደህንነትን ማረጋገጥ፣ በዘርፉ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

የፌዴራል የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካርያስ ኤርጉላ በበኩላቸው ተቋሙ የሀገሪቱን የፋይናንስ ደህንነት ለማረጋገጥ በኦፕሬሽንና ወንጀሎችን በጋራ መከላከል ላይ በትብብር እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በዚህም ሽብርን በገንዘብ መደገፍና በህገ ወጥ የተገኘውን ገንዘብና ሀብት ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጋራ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

”ህግን ማስከበርና ወንጀልን ከመከላከል አንፃር ከአገልግሎቱ ጋር በቅንጅት እንሰራለን” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ከፖሊስ፣ ከአቃቤ ህግ፣ ከባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሆን ተባብረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

መድረኩ የዘመኑን የቴክኖሎጂና ስልቶችን በመጠቀም በፋይናንስ ዙሪያ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በቅንጅት ለመከላከል ያግዛል ያሉት አቶ ዘካርያስ፣ ከፋይናንስ ውጭ በማዕድን፣ በብረታ ብረትና ሌሎች ሀብቶች ላይ ጭምር የሚፈፀሙ የማጭበርበርና የቅሸባ ወንጀሎችን ለመከላከል በጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

See also  በኬኒያ ናይሮቢ የተፈረመው የስምምነት ሰነድ (ኦሪጂናል ቅጂ) 

በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት፣ ከፍትህና ህግ ማስከበር የተውጣጡ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

Leave a Reply