ራሱን መሪ አልባ የሚያደርገው አማራ ክልል “በገፊና ጎታች” ሴራ በፖለቲካ ቧልት እየተበላው ነው

በጅምላ ማጠልሸት፣ ማሸማቀቅ፣ መግደልና ማስገደል፣ ባንዳዎችን፣ መሸተኞችንና ተላላኪዎችን ማግነን፣ ማሞገስ፣ ከፍ ማድረግ የአማራ ክልል ፖለቲካ መገለጫ ነው፤ ይህ አካሄድ ምራቃቸውን የዋጡ የክልሉ ተወላጆች ወደፊት እንዳይመጡ በፍርሃትና በስጋት ስላሸሻቸው ክልሉን ማንም እየተነሳ የሚጋልበው፣ የሚያንቦጫርቀውና የሚዘፍንበት አድርጎታል፤

የአማራ ክልል የራሱን መሪዎች በመብላት ሤራ ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በተለየ መታወቂያው ነው። የአማራ ክልል አሁን ላይ በፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ ሰዎች የሚገደሉበት ክልል ሆኗል። አማራ ክልል ላይ በተደጋጋሚ የሚስተዋለው መጠፋፋትና ይህንኑ በማወደስ የሚያራግቡት ክልሉን “ለፖለቲካ ቧልት” ዳርገውታል እየተባለ ነው።

የገፊና ጎታች ፖለቲካ መሃል ሜዳ” የሚባለው የአማራ ክልል መሪዎቹ እንዲገደሉ የሚያቅዱ፣ ግድያውን የሚያቀነባብሩ፣ ግድያውን የሚፈጽሙ፣ ግድያው ሲፈጸም ወደ ሌላ በመጠቆም ሕዝብ እንዲቆጣ የሚያደርጉ ተዋንያኖች የሚተራመሱበት እንደሆነ በርካታ መረጃ በማንሳት የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። ከሁሉም በላይ በፍረጃና ማጠልሸት ላይ አተኩረው የሚሠሩት ሚዲያዎች “የገፊና ጎታች” ፖለቲካው ፊት አውራሪዎች መሆናቸው ቀና ልቡና ባላቸው ዘንድ ፍርሃቻን ፈጥሯል።

ክልሉ እንደ ሌሎች ክልሎች ከለውጡ በኋላ ራሱን ማጽዳት ያልቻለ፣ በትህነግ ብብት ውስጥ የተወሸቁ የሤራ ቋቶችን ያላራገፈ፣ ግብስብሱን ይዞ ለመጓዝ የመረጠ መሆኑ ለበርካታ አሁናዊ ችግሮች ዳርገውታል። በዚህ አሳብ ዙሪያ “አሁን ድረስ ትህነግ ያሰፋለትን ባንዲራ ተብዬ ጥብቆ እንኳን መቀየር ያልቻለ” ሲሉ ክልሉን የሚመራውን ፓርቲ ይወቅሱታል። ይህ ያለመጥራቱ ማሳያ አንዱ በሽታ እንደሆነም ያሳያሉ።

የዶ/ር አምባቸው መኮነን፣ አቶ ምግባሩ ከበደ እና አቶ እዘዝ ዋሴና የአቶ ተስፋዬ ጌታቸው ግድያ እንዴት እንደተቀነባበረ፣ ማን እንዳቀነባበረው፣ ግድያው ለምን እንደተፈለገ፣ ወዘተ ገና ከጅምሩ ጀምሮ በገፊና ጎታች ፖለቲካ እንዴት ይነዳ እንደነበር የሚገልጹ “አማራ ክልል በሤራ መሪዎቹን እየበላ እዚህ ደረሰ” ሲሉ ክልሉ እንዴት ከድጡ ወደ ማጡ እንደተሽቀነጠረ ይገልጻሉ። መሪዎቹ እንዲበሉ የሚያደርጉትም ባንዳዎችና እንደሆኑ ይገልጻሉ።

መሪዎቹን የበላቸውን ወገን በማጀገን የሚዘመርበት የአማራ ክልል፣ ይህ ባንዳዎችን የማጀገን ስካሩ አልበርድ ብሎ ዛሬ ላይ አማራ ማንም የሚነዳው፣ ማንም የሚያንቦጫርቀው ፖለቲካ ሰላባ ለመሆን በቅቷል። እንደ ሕዝብ ተፈርጆ የሚደርስበት መከራና ሞት ሳያንሰው በሰላም በሚኖርበት ቀበሌው ማረስ እንዳይችል ሆኖ ሽፍታ ቀላቢ ሆኗል።

አማራ የሚመራው ብቁ ሰው ያጣ ይመስል የግድያው ተሳታፊና አራጋቢ በነበሩት የመሸታ ቤት ፖለቲከኞች እንዲመራ እየታዘዘ ነው። ይህን ግምገማ የሚሰጡ ወገኖች እንደሚሉት አማራ በየመድረኩ በሚያንዛርጡ ጨዋ መሳዮች፣ ራሳቸውን የአማራ መሪና ተቆርቋሪ ባደረጉ ባንዳዎች፣ የቀድሞ የትህነግ ተላላኪዎችና፣ ወልቃይትንና ጠገዴን ጨምሮ ፈርመው ለትህነግ እየገለፈጡ ባስረከቡ ከርሳሞች ያለ አንዳች ኃፍረት እንዲመራ የነዚሁ ወገኖች ተከፋይ በሆኑ ሚዲያዎች በሰበር ዜና እየደነቆረ ነው።

See also  ጄነራል አበባው - የመንደር ጄነራል አይደለሁም ... የአጥንት ፖለቲካ እንዲቀር ጥሪ አቀረቡ

አማራ ስም ተለጥፎበት፣ ተፈርጆ፣ በጅምላና በግል መከራ እንዲቀበል ተደርጓል፤ ይህ ሃቅ ነው። ከዚህ ግፍና መከራ ለመላቀቅ በሚል “ገፊና ጎታቾ ሴረኞችና ስምሪት ሰጪዎቻቸው ” በተቆርቋሪ ስም ሌላ የጥፋይ አጀንዳ እየሰፈሩለት ነው። “በእንቅርት ላይ…” እንዲሉ ይባስ ከሌላው ህዝብ የሚለየውን የቂም ካባ እየደረቡለት ነው። ልክ በትህነግ የውድቀት ስሌት አማራን ከወንድሞቹና ከወገኖቹ ለይተው የሴራቸው ሰለባ ለማድረግ በስሙ መርዝ እየረጩ ነው። ሌሎች መርዛማዎች ቢኖሩም አሁን ላይ አማራ ክልል ማንም እየተነሳ የሚያንቦጫርቀው፣ የሚንጠው፣ አረቄና ጠላ ቤት ተጋድመው ጀግና ነኝ የሚባሉበት፣ በስማ በለው ለሚንደቀደቀው ሁሉ ሴራውን እስከደገፈ ድረስ የሚዘመርበት፣ ዙሪያው በፖለቲካ ቧልት የጦዘ ክልል ሆኗል። ህዝብን ከመከራ ወደ መከራ የሚያሸጋግር፣ የጠላቶቹ መሳለቂያ ያደረገውና የያዘውን የሚያሳጣው መንገድ ላይ የጣለው ይህ አካሄድ አስተዋዮች በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሆነው ” ወዴት እየሄድን ነው? ምን ይሻላል? ቆም ብሎ ማሰብ ተሳነን? ማን እንዴት ይስማን?” እያሉ ነው። ምክንያቱም አማራ ክልል አስተዋይ፣ የረጋና ከሌሎች ጋር ህብረት ፈጥሮ የሚመራ፣ አዋቂና የሰከነ “ይወገድ” የአምቡላው መንደር ሰዎች ” ይንገሱ” የሚባልበት ለሰሚው ግራ የገባ ክልል ሆኗልና!

በተለይም በአሜሪካን ሜሪላንድ በሚኖሩ ባለቤትነት እንደተቋቋመ የሚነገርለትና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሻዕቢያ በጀት በሚደገፈው የመረጃ ቲቪ ተሳታፊ በሆኑ ዩቱበኞች የሚረጨው የከፋ ሤራ ክልሉን መንጋ እየተነሳ እንዲያወድመው ምክንያት እንደሆነ በስፋት መረጃዎች እየወጡ ነው።

“ያሳፍራል” ሲሉ የሚናገሩ “አማራን ክልል እንደ ዘመድኩን በቀለ ዓይነት አእምሮው ትክክል እንዳልሆነ የመሰከረ ቃልቻ በዚህ መልኩ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ ሲመራና የትግል አቅጣጫ ሲያዘጋጅለት ማየት የቁም ሞት ነው” ይላሉ። “ሻለቃ ዳዊትን ያክል በደም የተጨማለቀ ከሃጂ ባንዳ፣ እንደ ገዱ ዓይነት የአማራን ክልል ለትህነግ እየገለፈጠ ያስረከበ አለቅላቂ እና ሌሎችም አማራን ሊመሩ ሲደለቅላቸው መስማት ከቁም ሞትም በላይ ነው” ሲሉ ሃዘናቸውን ይገልጻሉ።

ሲቀጥሉም “እስክስታ ወራጁና ተወዛዋዡ የፖለቲካ ተንታኝና መሪ ሆኖ የተዋጊው ቡድን ቀለብ አልሰፍርም፣ ጥይት አልገዛም፣ ዘርፈህ ብላ” በሚል በገሃድ መዘባበቻ ያደረጉ ባዶዎች ሕዝቡን እንዴት ባለ ሞራል ሊመሩት እንዳሰቡ መገመት በራሱ ሕመም እንደሆነ ያስታውቃሉ።አበበ በለውና እንግዳዘር ነጋ

እነዚህ ወገኖች በዚህ አያበቁም፣ ሻዕቢያ የሚሰፍርላቸው ጋጋኖዎች በየወሩ እየተገላበጡ በሚረጩት የቀጣሪዎቻቸው ሤራ የአማራ ሕዝብ ችግሩን፣ በደሉን፣ የደረሰበትን ግፍ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሆኖ በአንድ ላይ እንዳይጋፈጥ ጠንቅ ሆነውበታል። ልክ ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ለይቶ ብቻቸውን እንዳስቀራቸው አማራም ልዩ ፍላጎት ያለው ሕዝብ አድርገው እየሳሉት ነው። በዚህም በመላው ኢትዮጵያ በሰላም የሚኖሩትን የአማራ ተወላጆች ሥጋት ላይ እየጣሉ ነው።

See also  ኢትዮጵያ ፌስቡክንና ትዊተርን ሊተካ የሚችል የማህበራዊ ትስስር ገጽ ስራ ላይ ልታውል ነው

የአማራን ለም መሬቶችና ርስት ተማምለው ያስረከቡ ባንዳዎች፣ ሕዝብን አስተባብረው ባንዶቹ የሰጡትን ርስት ያስመለሱትን ለመንቀፍ ሞራል የሌላቸው ከላይ በተዘረዘሩት ሚዲያዎች እየተሞካሹ ነው። እስኪ ዶ/ር ይልቃልን ወይም አቶ አገኘሁን ለመውቀስ አቶ ገዱ ምን ዓይነት የሞራል መሠረት አላቸው?” እርግጥ አሁን ባለው የክልሉ አመራር ውስጥ የገፊና ጎታች ሤራ አራማጆች ቢኖሩም በግርድፉ የቀደመው ብአዴን አብዛኛው አመራሮች ፍትህ ቢኖር ለፍርድ የሚቀርቡ በሆኑ ነበር።

ሁሉም ሆኖ አሁን ላይ አማራ ክልል በማጅራት መቺ፣ ባንዳና የመሸታ ቤት አለቅላቂዎች እንዲመራ የሚደረገው ትርምስ አካሄዱ ለገባቸው ሥጋት ሆኗል። የተለየ አሳብ ያላቸውን፣ በሰከነ ፖለቲካ ክልሉን ለማራመድ የሚፈለጉ፣ ችግርን ሳያሰፉ አማራ እንደ ሕዝብ ከደረሰበት ጉዳት አገግሞ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር መብቱና ጥቅሙ ተጠብቆለት እንዲኖር የሚመኙ አዳዲስም ሆኑ ነባር ቀና አሳቢዎችን የሚያሸማቀቀው፣ በግድያ ስንጠርዥ ውስጥ የሚያስከትተው የአማራ ፖለቲካ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል በርካቶችን አስጭንቋል።

“አስወግደው” የሚል መመሪያ የሚያስተላልፉ ሚዲያዎች ጥቆማ እየሰጡ ባለበት ባልተለመደ ሁኔታ ከአማራና ኦሮሞ መወለድ ወይም መቀላቀል “ሃፍ ካስት ነው” በሚያሰኝበት ሁኔታ፣ ይህም የሚያስገድል መሆኑ፣ የባለሃብቶች ስም እየጠተራ ሳይቀር በቀድሞ የኢህአዴግ አዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ መሪ ሃብታሙ አያሌውና የስኳር አክሲዮን ተዋናይ ምናላቸው ስማቸው አማካይነት ማስፈራሪያ በሚቀርብበት በዚህ ወቅት አማራን ማን ይምራ? ቁልፍ ጥያቄ ነው።

ምስክሮች እንደሚሉት ዶ/ር ይልቃል “በቃኝ” ካሉ ቆይቷል። ከእርሳቸው ቀደም ሲል አቶ አገኝሁ ክልሉን ለመምራት የተስማሙት በአጭር ጊዜ ውል ነበር። አሁን ላይ በርካታ ብቃት ያላቸው ጥያቄው ቀርቦላቸው አልፈለጉም። በሌሎች ክልሎች የሚፈለገውና እርስ በርስ የሚያቧጭቀው የክልል መስተዳድር መሪነት ቦታ በአማራ ክልል ግን ፈላጊ የለውም። በሌሎች ክልሎች እኔ ልምራ ባዩ ለቁጥር በሚያታክትበትና ሥልጣን ላይ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሮች ስዩመ እግዚአብሔር የሆኑ ይመስል ማንም እንዳይነቀንቃቸውና ቦታቸው እንዳይነጠቅ አጥብቀው ሲከላከሉ የአማራ መስተዳድር ግን የተሾመው “መቼ በተገላገልሁ” የሚልበትና “ተሹመሃል” ተብሎ የሚነገረውም “አልፈልግም” የሚልበት ወቅት ላይ ነው ያለው። በመሆኑም አሁን ላይ ክልሉን ዳግም ለማደራጀት እየተሠራ ባለው ሥራ ፈላጊ ያጣው የአመራር ቦታ ጉዳይ ፈታኝ እንደሆነ ይነገራል።

See also  በመላው ኢትዮጵያ መከላከያ አገርና ድንበር እንዲጠብቅ ስምሪት መቀበሉን መንግስት አስታወቀ

ተሹዋሚዎችን የሚያሳቅቀውና ብሎም የሚገድለው፤ በሌላ ጽንፍ ደግሞ “የአማራ ክልል መሪ እንዳይወጣበት ተደርጓል” እያለ በተመሳሳይ የሚደሰኩረው በአማራ ክልል የተጎነጎነው የገፊና ጎታ ሤራ የክልሉን መሪዎች እየበላ ክልሉን መሪ ዓልባ እያደረገ ያለው አካሄድ ካልቆመ የአማራ ክልል የከሸፈ ክልል (failed regional administration) እንደሚሆን ብዙ አመላካቾች አሉ።

በትግራይ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በተለይ ወጣት ያስጨፈጨፉት በምዕራቡ ዓለም ለጉብኝት ሲመጡ አዳራሽ ተለቅቆላቸው፣ ፈንዲሻ ፈንድቶላቸው፣ ቄጤማ ተጎዝጉዞላቸው፣ በእልልታ አቀባበል ሲደረግላቸው የአማራ ክልል አመራሮች በተገኘው ሚዲያ ሁሉ ያለማቋረጥ ይሸማቀቃሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ እንደ ሚዳቋ በጥይት ይታደናሉ። ይህንን መረን የለቀቀ ፖለቲካ የሚመራው ኃይል በተመሳሳይ መልኩ በየሚዲያው እየወጣ “ክልሉ ሆን ተብሎ መሪ ዓልባ እንዲሆን ተደረገ” እያለ የአፍዝ አደንግዝ ድቤውን ይመታል። ድንቁርና በረከት የሆነላቸውም ይህንን እየሰሙ እንደ ገደል ማሚቶ “ሼርና ላይክ” እያደረጉ ያስተጋቡታል።

ነገ አርብ በሚደረገው ስብሰባ አዳዲስ አመራር እንደሚመረጡ እየተነገረ ይገኛል። ገና ማን ምን ቦታ እንደተመረጠ ይፋ ሳይሆን የስም ማጠልሸቱና ማሸማቀቁ ተግባር ተጠናክሯል። ገና ወንበሩ ላይ ሳይቀመጡ “አስወግዷቸው” ባዩም ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ይህ በስካር ላይ የሚገኘውና በገፊና ጎታች ሤራ የተተበተውና የማንም አልፎ ሂያጅ የአረቄ ማኅበርተኛ መደዴ እመራዋለሁ የሚለው የአማራ ክልል ፖለቲካ በዚሁ ከቀጠለ የክልሉን ነዋሪ እጅግ ከፍተኛ የኅልውና አደጋ ውስጥ ይጥለዋል። በተለይ በእርሻ ወቅት ሆን ተብሎ የሚደረገው የክፋት ሤራ መቋጫ ካልተደረገለት የክልሉን ነዋሪ ቅስም በሚሰብር ሁኔታ የሌሎች ክልሎች ተመጽዋች እና ወደ ሌሎች ክልሎች ተሳዳጅ እንደሚያደርገው ለመገመት የፖለቲካ ልሒቅ መሆን አይጠይቅም። ይህም “የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላታችን ነው” ብሎ የተነሳውን አማራን በጠላትነት የመፈረጅና ቀጣይ ሕይወቱ የመሸማቀቅና የውርደት እንዲሆን ታስቦ የተዋቀረው የትህነግ የፖለቲካ ርዕዮት ፍጻሜ የሚያገኝበት ይሆናል።  

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ


Leave a Reply