‘ማል ማሊሳ’ !! መፍትሄው ምንድን ነው? ሃጫሉ

ስለፍቅር፣ አገር፣ውለታ፣ ትግል፣ ቤሰብና ወላጅ አልባ ሕጻናት አቀንቅኗል። “ዋሴ” ሲል በድርብ ትርጉም ያዜመላት ባለቤቱ ” ሃጫሉ አልሞተም” ማለቷ አግባብ ስለመሆኑ ስራው ይመሰክራል። ልከኛና አስተዋይዋ ባለቤቱ ” የሃጫሉን ስም አላግባብ አትጠቀሙ” ማለቷም ከዚህ ጥልቅ ስራው አንጻር ሲመዘን ሚዛን ይደፋል። ዛሬ ምንም የማያውቁ ሕጻናት ወላጅ አልባ ሆነው የማደጋቸው ጉዳይ ያሳሰበው ሃጫሉ ስለ እነሱም አዚሟል። ለልጆቹ ጭምር።

ሃጫሉን በተራ የፖለቲካ እምነት የሚያጥሩት እጅግ የተሳሳቱ መሆናቸውን አብርቶ የሚያሳየው ስራው ሃጫሉ ደግ፣ ለጋስ፣ የሕዝብ ስሜትን የሚረዳ፣ ለሕዝብ ስሜትና አሳብ የቀረበ፣ ያመነበትን በገሃድ የሚናገር፣ እንደ ዘመኑ የማይገላበጥ፣ ቆፍጣናና የማይደለል መሆኑን ከልጅነት ጀመሮ የሚያውቁት ይመስክሩለታል። ሳቂታና እጅግ ቀለደኛ እንደሆነ የሚተርኩት ወዳጆቹ ዛሬም አንስተውት አይጠግቡም።

የአገራችን የወንበር በሽታ ያጠናገረው ፖለቲካ ሃጫሉን እንዳይጠገብ አድረገው። ከሞቱና አሟሟቱ ይልቅ አስከሬኑንን ለግላቸው ጉዳይ ሊጠቀሙ በሞከሩ እያፈርን የሸኘነው ሃጫሉ ዛሬም በስራው በርቷል። ቢቢሲ የዘገበውን ከስር እንዳለ አትመነዋል።

በባለፈው ዓመት የተገደለው ሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ በኢንተርኔት ሙዚቃን በሚሸጠው አይቲዩንስ መቶ አልበሞች ውስጥ በአለም አቀፍ ሽያጭ ሰንጠረዥ ሦስተኛ ደረጃን በትናንትናው ዕለት ይዞ ነበር።

የአይቱዩንስ የዓለም የሙዚቃ ሰንጠረዥ (ወርልድ ቻርት) በየሰዓቱ የሚቀያየር ሲሆን ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል። በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት የሃጫሉ አልበም በዓለም አቀፍ ሽያጭ ሰንጠረዥ በ12ኛ ደረጃ መቀመጡን ከድረ-ገጹ ባገኘነው መረጃ መረዳት ተችሏል።

እንዲሁም ቢቢሲ በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ እንደተከታተለው አልበሙ በምርጥ 40 የአሜሪካ የፖፕ ሙዚቃ ዘርፍ በአይቲዩንስ በሽያጭ አንደኛ ደረጃ መቆጣጠሩን አመልክቷል።

ከትናንት በስቲያ ሰኔ 22/2013 ዓ.ም የወጣው ይህ አልበም ‘ማል ማሊሳ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ትርጉሙም “መፍትሄው ምንድን ነው?” የሚል ነው።

ማል ማሊሳ አስራ አራት ዘፈኖችን የያዘ አልበም ሲሆን የሙዚቀኛው ባለቤት ወይዘሮ ፋንቱ ደምሶ ከቢበሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ህይወቱ ከማለፉ በፊት የሰራቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህ አልበም ላይ አራቱ ከዚህ ቀደም ከሰራቸው ሁለት አልበሞች ተሻሽለው የተሰሩ፣ አስር አዳዲስ ሙዚቃዎች ተካተውበታል። ከአዳዲሶቹም ሙዚቃዎች ውስጥ የተወሰኑት ያልተጠናቀቁም እንደነበር ቢቢሲ የተረዳ ሲሆን ሃጫሉ ከሞተ ከአምስት ወራት በኋላ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ተገናኝው ሥራዎቹን በማሰባሰብ አልበም እንዲሆን ተደርጓል።

በዚህ አልበም ውስጥ የተካተቱት ዘፈኖች ግጥም ይዘት የፍቅር ዘፈኖችን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን ይዳስሳል።

የሃጫሉ አልበም

የአልበሙ መጠሪያ የሆነው ማል ማሊሳ ባለፉት መቶ ዓመታት የኦሮሞ ሕዝብ ያሳለፈውን ታሪክ፣ ትግል፣ መስዋዕትነት የሚዳስስ ሲሆን በአሁንም ወቅት መቀጠሉ “መፍትሄው ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ እንዳጫረበት በሙዚቃው መልዕክቱን አስተላልፏል። በዚህ ዘፈን ላይ በርካቶች ሞተው፣ ታግለው ሕዝብ ከጭቆና ሊላቀቅ ያለመቻሉን ጠቅሶ መቋጫ የሌለው ነገር እንዴት ሊሆን ቻለ በማለት ይጠይቃል።

በመጀመሪያ አልበሙ ላይ “ኦልማንኬ” (የአንቺ ውለታ) ብሎ የዘፈነላት ባለቤቱ ፋንቱ በዚህም አልበምምም ላይ “ሃደ ወቢ’ (የወቢ እናት) በሚልም ምስጋናውን አቅርቦላታል።

ወቢ የሚለው የኦሮምኛ ቃል ዋስ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን የመጀመሪያ ልጁም መጠሪያ ነው። በዚህም ሙዚቃው ልጁን በፀጋ እንደሰጠችውና እንዲሁም ዋስ እንደሆነችው በድርብ ትርጉም አካትቶታል። ከዚህም በተጨማሪ የህይወቴ ምሰሶ፣ መሰረቴ ነሽ ይላታል።

ይህንን አልበም የሰሙ ሰዎች አስተያየት እንደሚሰጡት በዚህ አልበም የፍቅርን ዘፈን ጨምሮ፣ ነፃነት፣ ትግልና በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን ወላጅ አልባ ህፃናትንም አስታውሷል።

“ኢልመ ነማ” የተሰኘውና (የሰው ልጅ) በአልበሙ ላይ የተካተተው ይህ ሙዚቃ ህፃናቱ አባትና እናት አልባ መሆናቸው አምላክ ያደረገው ነገር ቢሆንም ህፃናቱን መርዳትና ማስታወስ እንደሚያስፈልግ ምክሩን ይለግሳል።

በዚህም የአልበም ሥራው ላይ በርካታ ሙዚቀኞች የተሳተፉ ሲሆን ዘጠኙን በማቀናበር በርካታ የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን የሚያቀናብረው ዳዊት ታደሰ ተሳትፎበታል።

ከእሱም በተጨማሪ ካሙዙ ካሳ፣ ዲንቄሳ ደበላ፣ አብርሃም ኪዳኔ በአቀናባሪት የተሳተፉ ሲሆን አስራ አራቱንም ሙዚቃዎች ሚክስና ማስተር ያደረገው አበጋዝ ክብረ ወርቅ ሺዎታ ነው።

በባለፈው ዓመት የተገደለው ሃጫሉ ሁንዴሳ የኦሮሞ የትግል ሙዚቃዎችን በመዝፈን በርካቶችን ማነሳሳቱን እንዲሁም ጭቆናን በሙዚቃው የታገለ፤ ለነፃነት የሠራ በማለት ይመሰክሩለታል።

Leave a Reply