ኮድ 3 መኪና ስም ለማዞር ሻጭ የመኪናዉን ግምት 35% እንዲሁም ገዢ 15% እንዲከፍሉ ተወስኗል?

ባለፈዉ ሳምንት ኢትዮጵያ ቼክ “ኮድ 3 መኪና ስም ለማዞር ሻጭ የመኪናዉን ግምት 35% እንዲሁም ገዢ 15% እንዲከፍሉ ተወስኗል” የሚል ጥቆማ ደርሶት የመረጃዉን ትክክለኛነት የማጣራት ስራ ሰርቷል።

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን እንዲሁም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት /የቀድሞ ዉልና ማስረጃ/ ነበር ያናገረዉ።

ሁለቱም ተቋማት የተሽከርካሪ ባለቤትነት ስም ለማዞር ሻጭ የመኪናዉን ግምት 35% እንዲሁም ገዢ 15% ይከፍላሉ የሚባለዉ በተቋማቱ እንደሌለ ነግረዉን ነበር።

ኢትዮጵያ ቼክም ይህን መረጃ በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ካጋራ በሗላ ክፍያዉ ስም ለማዞር ከላይ ለተጠቀሱት ተቋማት የሚከፈል ሳይሆን ለገቢዎች የሚከፈል ታክስ መሆኑንና ጉዳዩንም እንድናጣራ ተጨማሪ ጥቆማ ደርሶናል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ቼክ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ክፍልን መረጃ የጠየቀ ሲሆን ክፍሉም ወደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ገ/ስላሴ መርቶናል።

“ስም ሲዞር በአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ተገምቶ /የመኪናዉ ዋጋ/ ወደኛ ተቋም ይመጣል” ያሉት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተቋማቸዉ በባለስልጣኑ ግምት ላይ ጥርጣሬ ካለዉ በራሱ አጥኚ ቡድን የመኪናዉን ዋጋ የማስገመት ስልጣን እንዳለዉና ይህም አዲስ አሰራር እንዳልሆነ ነግረዉናል።

“በአዋጅ 983/2008 አንቀጽ 3 ላይ ገቢዎች ባለስልጣን ጥርጣሬ ካለዉ ተሽከርካሪ ሊሆን ይችላል፤ መሬትም፤ ምንም ሊሆን ይችላል ማንኛዉም ንብረት ግምት ማጥናት ይችላል ይላል” ይላሉ አቶ ሲሳይ።

“የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ግምት ትክክል እንዳልሆነ ግብር ከፋዮቻችንም /መኪና ሻጮች/ ያምናሉ። ለምን እንደዚህ አደረጋቹ ብልን ስንጠይቃቸዉ የቆየ ሲስተም አለን በዛ ሲስተም ነዉ የምንጠቀመዉ የሚል ምላሽ ነዉ የሚሰጡን” ብለዋል።

አዋጁ በ2008 ከወጣ እስካሁን ለምን ስራ ላይ ሳይዉል ቆየ ብለን ለጠየቅናቻዉ ጥያቄ “ዋናዉ መስሪያ ቤት አጥንቶ ነዉ አሁን ወደትግበራ እንድንገባ ያደረገን” ብለዋል።

በተደረገዉ ጥናትም ከተማ አስተዳደሩ በመኪና ሽያጭ ብቻ በአመት 4.5 ቢልየን ብር እንደሚያጣና አሁን በኮድ 3 መኪኖች ላይ እየተገበረ የሚገኘዉ 35% ከንብረት የሚገኝ ገቢ ታክስ መነሻም ከተማ አስተዳደሩ የሚያጣዉ ገንዘብ እንደሆን አቶ ሲሳይ ይናገራሉ።

“ማንኛዉም ሰዉ ንብረቱን በሚያስተላልፍበት ወቅት ዋጋዉ መጀመሪያ ከነበረዉ በላይ ከሆነ ትርፍ በሆነዉ ብር ላይ 35% ታክስ ይጣላል” ብለዋል።

ለምሳሌ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአንድን ኮድ 3 መኪና ዋጋ አንድ ሚሊዮን ብር ብሎ ከገመተ ገቢዎች ደግሞ 1.2 ሚሊዮን ብሎ ከገመተ በሁለቱ ተቋማት ግምት መሀከል የ200 ሺህ ብር ልዩነት ይኖራል። ስለዚህ መኪና ሻጩ የ200 ሺህ ብር 35% ስሌት 70 ሺህ ብር ታክስ ለገቢዎች ይከፍላል ማለት ነዉ።

በተጨማሪም ለስም ማዞሪያ 2% ለገቢዎች እንደሚከፈልም የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ገ/ስላሴ ነግረዉናል።

EthiopiaCheck Update

Leave a Reply