መልዕክት ለክቡር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የአብክመ ፕሬዝደንት

ክቡር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ አመራር ዋና ትኩረት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች “ሀገራችን” ብለው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሠላምና ደህንነት ጉዳይ መሆኑን በአመራርዎ ማረጋገጥ (ልዩ ትኩረት መስጠት) ከቻሉ በአማራ የአመራር ታሪክ ቀዳሚው ይሆናሉ። በዚህ አቅጣጫ እስከቀጠሉ ድረስ ድጋፊዎ ብዙ ነው።

በመጨረሻም ለአማራ ህዝብ ያለኝ መልዕክት አሁን የሚሻለው የክልሉን መንግሥት በተለይም ፕሬዝዳንቱን በመደገፍ፣ የሆነ ታሪክ እንዲስሩ ከጎናቸው እንቁም። መንግሥት አልባ ሆኖ ከመታገል መዋቅር ይዞ መታገል የሚፈጥረውን አቅም ልብ እንበል።

በሹመትዎ ዕለት እንደገለፅኩት እርስዎ ወደ ሥልጣን የመጡበት ወቅት እጅግ አሰቸጋሪ ነው። እርስዎን ቀርቤ የመጨዋወት ዕድሉ ስለገጠመኝ አውቄወታለሁ፣ አጋዥ ቢያገኙ ለአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ዋጋ ያለዎት ሀገር ወዳድ መሪ እንደሆኑ፣ ቀናዒነትዎን ረዘም ያለ ስዓት ወስደን በተጨዋወትንበት ወቅት ግንዛቤ አግኝቻለሁ።

ያም ሆነ ይህ የታሪክ ዕዳ ሆኖ ሌሎች ሲያበላሹት የከረሙትን የአማራ ፖለቲካ እንዲመሩ ግዙፍ ኃላፊነት ተሸክመዋል። በተንከባላይ ውርስ ዕዳ የጎበጠ ክልል እንደተረከቡ አሁንም አምናለሁ። በዚህም የእርስዎ ጭንቀት ይታየኛል። እሳት ውስጥ እንደተጣዱ ስለማውቅ።

ለሁሉም የዛሬ መልዕክቴ አጭር ናት። ይሄውም ካሁን በኋላ የአማራ ክልል መንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ የአማራን ህዝብ በተለይም በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለውን አማራ ደህንነት ማረጋገጥ ላይ ቢሆን ይመከራል።

እርስዎም እንደሚያውቁትና እንደሚያምኑት ከፊሉ የአማራ ህዝብ አማራ ከሚባለው “ክልል” ውጭ ይኖራል። በተለይም በኦሮምያ፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ክልሎች። ስለ እውነት እንነጋገር ከተባለ ድኀረ-1983 ለተከታታይ 30 ዓመታት አማራ ተገደለ፣ ተሰደደ፣ ተዘረፈ የሚባል ዜና በየትኛው ዓመት ነው ያልተሰማው?

ከመጋቢት/2010 የአመራር ለውጥ ወዲህ ባለው ጊዜ ደግሞ አማራ የሥርዓታዊ ቅራኔ ማወራረጃ ተደርጎ፣ ከወንበር ተገፋሁ ያለ ሁሉ በአማራው ላይ ገጀራ ሲያነሳ ታይቷል። ሌሎች ደግሞ በአማራው ደም ወንበር ማጥበቂያ ሊያደርጉት ፈልገው “ተከበብኩ” ባሉ ቅፅበት አማራ እንደቅጠል ረግፏል፤ ንብረቱም ወድሟል። አንድ አርቲስት በሰው እጅ ሕይወቱ ማለፉን ተከትሎ፣ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የሌለ እስኪመስል ድረስ አማራው የሚታደገው አጥቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የሞት ፅዋን ተገንጭተው በአሰቃቂ ሁኔታ አልፈዋል።

See also  “ለኢትዮጵያ የተዘረጋው ወጥመድ ከወዲሁ እየተበጣጠሰ ነው”

ይህ ጭፍጨፋ በጊዜና በሁኔታዎች ሳይገደብ ምክንያት እየቀያየረ “ሀገራችን” ብለው የሚኖሩ ንፁሃን አማሮችን እየበላ እዚህ ደርሰናል።

አሁን ግን የግፍ ፅዋው ሞልቶ በመፍሰስ ላይ ነው። ሞትን የተላመድ የሚመስለው ሕዝብ የቁጣው ዕቶን እየተንቀለቀለ ነው።

ስለሆነም ካሁን በኋላ የአማራ ክልል መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ሁነኛ እልባት ሳያበጅ/ሳያስበጅ “በክልሌ ታጥሬ ነው የምመራ” የሚል እሳቤውን ካስቀጠለ፣ ችግር ሊከሰት ይችላል። ችግሩም እንዲህ በቀላሉ ሊወጡት የሚችል አይደለም። ምሬት አፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ሕዝቡን አስጨንቆታል። በዚህ የቁጣ ስሜት ወደጎዳና የሚወጣ ሕዝብ የትኛውም ኃይል ሊያቆመው አይችልም።

ስለሆነም አንዴ ተንከባላይ ውርስ ዕዳ ተሸክመዋልና ቁርጠኛ አመራር ማረጋገጥ ይጠበቅብዎታል።

ቀዳሚው ነገር የኮምዩኒኬሽን ቃል አጠቃቀም ከመቀየር ቢጀምር እመክራለሁ። “ከክልሉ ውጭ” የሚኖረው የአማራ ተወላጅ የሚለው አገላለፅ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የአማራ ተወላጆች በሚል ቢታረም ይመከራል።

ይህ የክልል አወቃቀር የዛሬ ሠላሳ ዓመት የመጣ ቢሆንም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉ የአማራ ተወላጆች “ሀገራችን” ብለው መኖር ከጀመሩ ሃምሳና ስልሳ አንዳንድ አካባቢዎች ከዚያ በላይ ያስቆጠሩና ቅድመ አያቶቻቸውም በዚያው ቦታ ኑረው በሕይወት ያለፉ ይገኙበታል።

ይሄንን እውነታ ያገናዘበ የፖለቲካ ኮምዩኒኬሽን ያስፈልጋል። ትላንት በተተከለ የብሔር አጥር ውስጥ እንዲፈረጁና እንደመጤ እንዲቆጠሩ መፍቀድ አይገባም። ታሪክ ወደ ኋላ ይቆጠር ቢባል እውነት መቆማዊያው የት ጋ እንደሚሆን ለማናችንም አይሰወርም። ይህም ሆኖ ዛሬም ሀገራዊ አንድነት መዳኛችን ስለመሆኑ አማራው ያምናል።

ነገር ግን አብሮነት ህልውናን ከማስከበር ይጀምራል። ወንድማማችነት ከመልካም ጉርብትና፣ ከጋራ ዕጣ ፈንታ ይመነጫል።

አፋቸውን በኦሮምኛ ቋንቋ የፈቱ ለጋ ህፃናትን ደምና አጥንት ወገኋላ ቆጥሮ የፖለቲካ ቅራኔ ማወራረጃ የሚያደርጉ ኃይሎች አራት ዓመት ሙሉ በሕግ ማስከበር ዘመቻ ፅድተው አለማለቃቸው ጉዳዩን “ከዘር ማፅዳት ፕሮጀክት” ጋር ብናያይዘው ስህተት ሊሆን የሚችልበት አግባብ አይታየኝም።

ለዚህ ደግሞ አሁንም መሰል ድርጊቶች ያለማቋረጥ ከሚፈፀሙበት የክልልም ሆነ የፌዴራል አመራሮች ጋር በግልፅ መነጋገር የግድ ይላል። የሰበብ ፖለቲካ ሊሰበር ይገባል። የአመራር ተጠያቂነት ካልተረጋገጠ “ፕሮጀክቱ” ለኢትዮጵያ አደጋ ያዘለ ነው። የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጡ በሚገባቸው መሰል ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሊያሳልፍ ይገባል።

See also  …የሌብነት እጆች ሁሉ ይቆረጡ!

የሆነው ሆኖ የክቡር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ አመራር ዋና ትኩረት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች “ሀገራችን” ብለው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሠላምና ደህንነት ጉዳይ መሆኑን በአመራርዎ ማረጋገጥ (ልዩ ትኩረት መስጠት) ከቻሉ በአማራ የአመራር ታሪክ ቀዳሚው ይሆናሉ። በዚህ አቅጣጫ እስከቀጠሉ ድረስ ድጋፊዎ ብዙ ነው።

በመጨረሻም ለአማራ ህዝብ ያለኝ መልዕክት አሁን የሚሻለው የክልሉን መንግሥት በተለይም ፕሬዝዳንቱን በመደገፍ፣ የሆነ ታሪክ እንዲስሩ ከጎናቸው እንቁም። መንግሥት አልባ ሆኖ ከመታገል መዋቅር ይዞ መታገል የሚፈጥረውን አቅም ልብ እንበል።

ፕሬዝዳንታችንም፥ፅናትና ድፍረቱን ይስጥዎት!

Leave a Reply